በጉጂ ዞኖች ግጭት አሠቃቂ የሰብአዊ መብቶች ረገጣ ተባብሶ መቀጠሉን ካርድ አስታወቀ

Your browser doesn’t support HTML5

በጉጂ ዞኖች ግጭት አሠቃቂ የሰብአዊ መብቶች ረገጣ ተባብሶ መቀጠሉን ካርድ አስታወቀ

በሁለቱ የጉጂ ዞኖች ለዓመታት በቀጠለው ግጭት ሳቢያ፣ አሠቃቂ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት እየተፈጸመ መኾኑን የገለጸው የመብቶች እና የዴሞክራሲ እድገት ማዕከል በምኅጻሩ ካርድ፣ ለዞኖቹ ነዋሪዎች የሰላም፣ የፍትሕ እና የተጠያቂነት ርምጃዎች እንዲወሰዱ ጥሪ አቀረበ፡፡

የመብቶች ተሟጋቹ፣ ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ባወጣው መግለጫ፣ በመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች እና በታጣቂዎች መካከል ለዓመታት እንደዘለቀ በገለጸው “ነውጥ አዘል ግጭት” ሳቢያ፣ በዞኖቹ ነዋሪዎች ላይ የደረሱ ሠቆቃዎችን ያሳያሉ ያላቸውን 36 የማሳያ ታሪኮች በጥናታዊ ሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡

SEE ALSO: በምዕራብ ጉጂ ዞን ግጭት አራት ሰዎች መገደላቸውን ወረዳው አስታወቀ

ሁለቱን የጉጂ ዞኖች ጨምሮ በኦሮሚያ ምዕራባዊ ዞኖች፣ በትግራይ፣ በዐማራ እና በቤንሻንጉል ጉምዝ ክልሎች በቀጠሉ ግጭቶች እና ግጭቶቹ ባስከተሏቸው ጫናዎች፣ አዎንታዊ ለውጥ ይመጣል ብሎ እንደማያምን የገለጸው ካርድ፣ ዘላቂ መፍትሔ ለማግኘት፥ ሐቀኛ እና አሳታፊ ድርድሮች እንዲደረጉ፣ በነውጥ አዘል ግጭቶች ጉዳት የደረሰባቸው ዜጎች ፍትሕ እንዲያገኙ፣ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ፈጻሚዎች ተጠያቂ እንዲኾኑ ለሁሉም ባለድርሻ አካላት ጥሪ አቅርቧል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በጉጂ እና ምዕራብ ጉጂ ዞኖች፣ በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች መካከል ለዓመታት በቀጠለው ግጭት፣ የዜጎች መደበኛ ሕይወት መቋረጡን የገለጸው የመብቶች እና የዴሞክራሲ እድገት ማእከል በምኅጻሩ ካርድ፣ በዞኖቹ ነዋሪዎች ላይ ይፈጸማሉ ባላቸው አሠቃቂ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ላይ ያካሔደውን ጥናታዊ ሪፖርት፣ ከትላንት በስቲያ ቅዳሜ ይፋ አድርጓል፡፡

Your browser doesn’t support HTML5

በጉጂ ዞኖች ግጭት አሠቃቂ የሰብአዊ መብቶች ረገጣ ተባብሶ መቀጠሉን ካርድ አስታወቀ

በነዋሪዎቹ ላይ ይደርሳሉ ያላቸው የሰብአዊ መብቶች ጥሰት ተገቢ ትኩረት አለማግኘታቸውን የገለጸው ማዕከሉ፣ ሠቆቃዎቹን ለብዙኀን ለማድረስ ያስችላሉ ያላቸውን 36 የማሳያ ታሪኮች በመሰብሰብ በጥናታዊ ሪፖርቱ ይፋ ማድረጉን፣ ዋና ዲሬክተሩ በፈቃዱ ዘኀይሉ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል፡፡

በአፋን ኦሮሞ፣ በዐማርኛ እና በእንግሊዘኛ ቋንቋዎች የቀረቡት የማሳያ ታሪኮቹ፣ በግጭት ውስጥ በገቡት በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት እና በመንግሥት የጸጥታ ኀይሎች፡- በዞኖቹ ነዋሪዎች ላይ ከሕግ ውጪ ግድያዎች፣ የዘፈቀደ እና የጅምላ እስሮች፣ ጾታን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች፣ የንብረት ውድመት፣ አስገድዶ የመሰወርና የገንዘብ ማግኛ እገታ ድርጊቶች፣ የማሠቃየት እና ኢሰብአዊ አያያዝ የመፈፀም፣ እንዲሁም የማፈናቀል ድርጊት እንደሚፈጸሙ አትቷል፡፡

አቶ አዱላ ጩሉቄ የጎሮ ዶላ ነዋሪ ናቸው፡፡ አሁንም ቀጥሏል ባሉት ግጭት፣ ገፈት ቀማሹ ነዋሪ መኾኑንና በችግር ላይ እንደሚገኝ አስረድተዋል።

በጥናታዊ ሪፖርቱ ውስጥ በተካተተው ጾታን መሠረት ባደረገ ጥቃት ላይ፣ የሥነ ጾታ አጥኚዋ ናርዶስ ጩታ አስተያየታቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ሰጥተዋል፡፡

የሥነ ጾታ አጥኚዋ፣ ሁለቱም ተፋላሚ ኀይሎች ወደ መፍትሔ መጥተው፣ ለነዋሪው ሠቆቃ እልባት እንዲያበጁ ጠይቀዋል፡፡

የመብቶች እና የዴሞክራሲ እድገት ማእከል ፕሮጀክት ኃላፊ የኾኑት ዓለማየሁ ተሾመ ደግሞ፣ ግጭቱ፣ ከነዋሪዎች ሠቆቃ በተጨማሪ፣ በጉጂ አሉ በተባሉት የተፈጥሮ ማዕድናት አገሪቱ እንዳትጠቀም እንቅፋት ኾኗል፤ ብለዋል።

የመብቶች እና የዴሞክራሲ እድገት ማእከል - ካርድ፣ በጥናታዊ ሪፖርቱ ባቀረበው ምክረ ሐሳብ፣ ሁለቱም ተፋላሚ ኀይሎች፣ በግጭት ወቅት ለሰላማዊ ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉ፣ ገለልተኛ ሲል የገለጻቸው የኢትዮጵያ እና የተባበሩት መንግሥታት ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽኖች፥ በነውጥ አዘሉ ግጭት የደረሰውን ጉዳት እንዲመረምሩና ተጠያቂነትን እንዲያረጋግጡ፣ ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ርዳታ እንዲቀርብ ጠይቋል፡፡

በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል የቀጠለው ነውጥ አዘል ግጭትም፣ በፖለቲካ ዉይይት ለመቋጨት ያለመ ድርድር ዳግም እንዲቀጥልም ጥሪ አቅርቧል፡፡

የመብቶች እና የዴሞክራሲ እድገት ማእከል በጥናታዊ ሪፖርቱ ስላቀረባቸው የሰላም፣ የፍትሕ እና የተጠያቂነት ጥሪ፣ ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት እና ከክልሉ ፍትሕ ቢሮ፣ እንዲሁም ከኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡