የአውሮፓ ኅብረት በመርዓዊ የሲቪሎች ግድያ እንዲመረመር ጠየቀ

  • ቪኦኤ ዜና

መርዓዊ ከተማ

የአውሮፓ ኅብረት በአማራ ክልል መርዓዊ ከተማ ላይ የተፈጸመው ግድያ እጅግ እንዳሳስበው ገልጾ፣ በገለልተኛ ወገን እንዲመረመር ጠይቋል።

የኅብረቱ ቃል አቀባይ ናቢላ ማስራሊ ትናንት ባወጡት መግለጫ፣ በክልሉ የተራዘመው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ አሳሳቢ ጉዳይ መሁኑን እና በክልሉ የሚገኙትን ሕዝቦች የሰብዓዊ መብት በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚገድብ ገልጸዋል።

“በአሁኑ ወቅት ለሚታየው ግጭት ፖለቲካዊ መፍትሄ ለመሻት፤ የንግግር፣ የእርቅና የሰላም ሂደት ለመጀመር የሚደረጉ ጥረቶችን ለማገዝ ኅብረቱ ያለውን ዝግጁነት በድጋሚ ያረጋግጣል” ብለዋል ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው።

“ኢትዮጵያውያኖች የውይይትን መንገድ እንዲመርጡ እናበረታታለን። በአገሪቱ የሚታዩትን ግጭቶች በዘላቂነት የሚያቆመው ሰላማዊ መፍትሄ ብቻ ነው” ብሏል ኅብረቱ በመግለጫው።

SEE ALSO: በመርዓዊ ቢያንስ 45 ሲቪሎች በመንግሥት ኃይሎች መገደላቸውን ኢሰመኮ ገለጸ

የመርዓዊ ከተማን ጨምሮ በአማራ ክልል ሦስት ስፍራዎች፣ ባለፈው ጥር ወር በትንሹ 66 ሰዎች በመንግሥት ኃይሎች እንደተገደሉ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን በትናንትናው ዕለት ማስታወቁ ይታወሳል።

በመርዓዊው ጥቃት፣ “ለፋኖ ድጋፍ አድርጋችኋል” በሚል ከተገደሉት ቢያንስ 45 ሲቪሎች በተጨማሪ፣ “የፋኖ አባላት ናቸው” በሚል የተጠረጠሩ ሰዎችም እንደተገደሉ ኮሚሽኑ ገልጿል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ጉባኤ (ኢሰመጉ) በበኩሉ ባለፈው ማክሰኞ ባወጣው መግለጫ፣ በመርዓዊ ከተማ በፌዴራል ኃይሎችና በክልሉ በሚገኙ ታጣቂዎች መካከል የተከሰተውን ግጭት ተከትሎ፣ የፌዴራሉ ኃይል ዓባላት ቤት ለቤት በምዘዋወር እና በጅምላ በተፈፀመ ግድያ ከ80 በላይ ሲቪሎች እንደተገደሉ አስታውቋል።

የኢሰመጉን መግለጫ ተከትሎ፣ የአሜሪካ መንግስት ግድያውን አስመልክቶ በወጡት ሪፖርቶች ላይ ምርመራ እንዲደርግ ጠይቋል።

“ከአማራ ክልል መርዓዊ ከተማ የወጡትና ሲቪሎችን ኢላማ ያደረጉ የግድያ ሪፖርቶች፣ የአሜሪካ መንግስትን በእጅጉ ያሳስበዋል” ሲሉ በኢትዮጵያ የአሜሪካ አምባሳደር ኧርቪን ማሲንጋ ባለፈው ዓርብ ገልጸዋል።

“የሰብዓዊ መብት መርማሪዎች ካለገደብ በአካባቢው ገለልተኛ ምርመራ እንዲያደርጉ፣ ግድያ የፈጸሙትም ለፍርድ እንዲቀርቡ” ሲሉ አምባሳደሩ ጥሪ አድርገዋል።