በሁለት ዓመቱ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ “ግፍ ተፈጽሟል” በሚል ምክንያት ለሦስት ዓመታት ያህል ርዳታውን አቋርጦ የነበረው የአውሮፓ ኅብረት፣ 650 ሚሊዮን ዩሮ ለኢትዮጵያ እንደሚለግስ፣ ትላንት ማክሰኞ አስታውቋል።
በአውሮፓ ኅብረት የዓለም አቀፍ ትብብር ኮሚሽነር ዩታ አርፕሌነን፣ ከኢትዮጵያው የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ጋራ በመኾን፣ ትላንት ማክሰኞ፣ በዐዲስ አበባ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ርዳታው እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።
ኮሚሽነሯ፣ “ቀስ በቀስ ግንኙነታችንን ለማሻሻልና ትብብራችንን ለማጠናከር ጊዜው አሁን ነው፤” ብለዋል። አያይዘውም፣ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት፣ ባለፈው ጥቅምት በፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ካበቃ በኋላ፣ ርዳታው፥ “የመጀመሪያው ተጨባጭ ርምጃ” እንደኾነ ገልጸውታል፡፡
የአውሮፓ ኅብረት፣ እ.አ.አ ከ2021 እስከ 2027 ሊሰጥ የነበረው ገንዘብ አንድ ቢሊዮን ዩሮ እንደነበረ፣ ጦርነቱ መፈንዳቱን ተከትሎ በ2020 መጨረሻ ርዳታውን አቋርጧል።
ርዳታው፣ ከጦርነት ለማገገም የሚደረገውን ጥረት እንደሚያግዝና የኢኮኖሚ ተሐድሶን እንደሚያሳልጥ፣ የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ተናግረዋል። ለአገሪቱ “ወሳኝ በኾነ ወቅት” የመጣ ርዳታ ነው፤ ሲሉም አክለዋል።
ለአገሪቱ መንግሥት በቀጥታ የሚሰጠው የበጀት ድጋፍ ግን፣ “ግልጽ የፖለቲካ ኹኔታዎች” እስኪሟሉ እንደተቋረጠ እንደሚቆይ፣ ዩታ አርፕሌነን አስታውቀዋል። ኮሚሽነሯ፣ በጉዳዩ ላይ ዝርዝር ጉዳዮችን አላነሡም። ኾኖም በቅድሚያ፣ ከዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት(IMF) ፕሮግራም መኖሩ አስፈላጊ ነው፤ ሲሉም አክለዋል።
ዩታ አርፕሌነን፣ ትላንት ማክሰኞ፣ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋራ ተገናኝተው ተነጋግረዋል።
የአውሮፓ ኅብረት ርዳታ የመጣው፥ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብት ኮሚሽን ባለሞያዎች፣ በጦርነቱ ወቅት በተፈጸሙ ጥሰቶች ላይ የሚያደርጉት ምርመራ ይራዘም እንደኹ ድምፅ ከመስጠቱ አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነው።
ባለሞያዎቹ ትላንት በሰጡት መግለጫ፣ “ወደፊት ግፍ የመፈጸም ዕድል በመኖሩ፣ በኢትዮጵያ ተጨማሪ ገለልተኛ ምርመራ መደረጉ አስፈላጊ ነው፤” ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
በትግራይ ክልል “ከባድ እና እየቀጠለ ያለ” ግፍ በመፈጸም ላይ እንደኾነ፣ ባለፈው ወር ያስታወቀው የመንግሥታቱ ድርጅት የምርመራ ቡድን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ተጠያቂነትን ለማስፈን ያለውን ቁርጠኝነት አስመልክቶ ጥያቄ አንሥቷል።
SEE ALSO: ተመድ የኢትዮጵያ መርማሪ ቡድኑን የሥራ ጊዜ እንዲያራዝም ሂዩማን ራይትስ ዎች ጠየቀሂዩማን ራይትስ ዎች በበኩሉ፣ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮያ በተፈጸመው ግፍ ላይ የሚደረገው ምርመራ እንዲቀጥል፣ የአውሮፓ ኅብረት ለተመድ የሰብአዊ መብት ም/ቤት ጥያቄ ማቅረብ አለበት ሲል አስታውቋል። “ያን አለማድረግ የራሱን ቃል እንደማጠፍ ይቆጠራል፤” ብሏል የሰብአዊ መብት ድርጅቱ።