በኦሮምያ የተለያዩ አካባቢዎች ዛሬም የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩና በአንዳንድ አካባቢዎች ግጭትም መስተዋሉ ተሰምቷል፡፡
ነቀምት አካባቢ በተኩስ ልውውጥ የታጀበ ግጭት እንደነበረ፣ በምሥራቅ ሸዋ ጉደር አካባቢ ደግሞ ትናንት ምሽት ላይ በተቃዋሚዎች እና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በተነሣ ግጭት የሁለት ሰው ሕይወት መጥፋቱና ውጥረቱ አሁንም እንደበረታ መሆኑን የቪኦኤ አፋን ኦሮሞ ዝግጅት ክፍል ባልደረባ ናሞ ዳንዲ ወደየአካባቢው እየደወለ ካሰባሰባቸውና በየማኅበራዊ መገናኛው እየወጡ ካሉ መረጃዎች ለማወቅ ተችሏል፡፡
በጉደር፣ በአምቦ፣ በቶኬ ወረዳ ቶኬ ከተማና በጎሮ ሶሌም እንዲሁ ግርግርና ግጭቶች እንደነበሩ ተገልጿል፡፡
ጉዳር ውስጥ ትናንት ምሽት ላይ በነበረ ግጭት የሁለት ሰው ሕይወት ጠፍቷል ተብሏል፡፡
በሌላ በኩል ደግሞ በምሥራቅ ሃገርጌ ግራዋም ግጭቶች የነበሩ ሲሆን ደቡብ ኦሮምያ ውስጥም የአባባቢው ነዋሪዎች ለአንድ ባለሃብት ተሰጥቶ የነበረን አንድ ሺህ ሄክታር የሚሆን መሬት እራሣቸው በሽማግሌ መከፋፈላቸውን ናሞ ያነጋገራቸው የአካባቢው ሰዎች ገልፀዋል፡፡
ነገሌ ከተማ ውስጥ ዛሬ ተደርጎ የነበረ ሰልፍ ያለ ግጭት መበተኑም ተገልጿል፡፡
በአርሲና በሌሎችም አካባቢዎች ተመሣሣይ እንቅስቃሴዎች እንደነበሩም ተሰምቷል፡፡
መንግሥት ሁኔታውን በቁጥጥር ሥር ያዋለ መሆኑን በቀደሙ መግለጫዎቻቸው የተናገሩት የኢትዮጵያ የመንግሥት ኮምዩኒኬሽንስ ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትሩ አቶ ጌታቸው ረዳ ለቪኦኤ በሰጡት ቃል ኦሮምያ ውስጥ ከተፈጠረው ሁኔታ ጋር ከታሠሩት ሰዎች ምርመራ ተካሂዶ ወንጀል የሌለባቸው እንደሚለቀቁ ተናግረዋል፡፡
ነፍስ ያለአግባብ የቀጠፉ ሰዎች የመንግሥትም ይሁኑ የሌላ ወገን ለፍርድ እንደሚቀርቡ ሚኒስትሩ ገልፀዋል፡፡
ለተጨማሪ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡
Your browser doesn’t support HTML5