በኢትዮጵያና በሶማሊላንድ መሪዎች መካከል ትናንት የተፈረመውን ኢትዮጵያ የባሕር በር የምታገኝበት የመግባቢያ ሠነድ ተከትሎ ሶማሊያ በኢትዮጵያ የሚገኙ አምባሳደሯን ጠርታለች፡፡
ሶማሊያ አምባሳደሯን አብዱላሂ ዋርፋን የጠራቻቸው ስምምነቱን አስመልክቶ ዛሬ አስቸኳይ የካቢኔ ስብሰባ ካካሄደች በኋላ ሲሆን ከስብሰባው በኋላ ባወጣችው መግለጫ “በማንኛውም ህጋዊ መንገድ” ግዛቷን እንደምትከላከል አስታውቃለች፡፡
የሶማሊያ ፌደራል መንግሥት ባስተላለፈው ባለ 9 አንቀጽ የውሳኔ ሃሳብ ኢትዮጲያ እና ራስ ገዟ ሶማሊላንድ ትናንት የደረሱት ስምምነት “ሕጋዊ መሠረት የሌለው እና ተፈጻሚ ሊሆን የማይችል ነው” ብሏል፡፡
ስምምነቱ ለ50 ዓመት የሚዘልቅ ሊዝ እና እየታደሰ የሚቀጥል መሆኑን ትናንት የገለፁት የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ሚኒስትር ሬድዋን ሁሴን ኢትዮጵያ ሶማሌላንድ ውስጥ የጦርና የንግድ ሠፈር እንዲኖራት የሚፈቅድ መሆኑንም ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ወደ አደን ባሕረ ሰላጤ የባሕር በር ልታገኝ የምትችልበትን የመግባቢያ ሠነድ ትናንት ታህሳስ 22 / 2016 ዓ.ም. አዲስ አባባ ላይ የፈረሙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና እንደሃገር ዓለም አቀፍ ዕውቅና የሌላት የሶማሌላንድ ፕሬዝደንት ሙሴ ቢሂ አብዱ ናቸው።
የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ፅህፈት ቤታቸው ውስጥ ከተከናወነው የፊርማ ሥርዓት በኋላ በሰጡት አስተያየት “ስምምነቱ ከኢትዮጵያ ጉልህ ስብራቶች መካከል አንዱን የሚጠግን ነው” ብለዋል፡፡