የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን፣ በአይቮሪ ኮስት በመካሄድ ላይ ባለው የአፍሪካ ዋንጫ የእግር ኳስ ውድድር ላይ ትናንት ሰኞ በመገኘት፣ አስተናጋጅዋ አይቮሪ ኮስት ከኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር የነበረባትን ግጥሚያ ተመልክተዋል።
በምዕራብ እና በመካከለኛው አፍሪካ ባሉ አራት አገራት ጉብኝት በማድረግ ላይ ያሉት ብሊንከን፣ ትናንት ሰኞ ኬፕ ቨርድ ጎራ ብለው የነበረ ሲሆን፣ ከዛም በተመሳሳይ ቀን ወደ አይቮሪ ኮስት አቅንተው ነበር። በመዲናዋ አቢጃን እንደደረሱም፣ አገሪቱ ከኢኳቶሪያል ጊኒ ጋር የነበረባትን የመጨረሻ የምድብ ጨዋታ በማከናወን ላይ ወዳለችበት ስቴዲየም አምርተዋል። በጨዋታው ትንሿ አገር ኢኳቶሪያል ጊኒ አስተናጋጇን አይቮሪ ኮስት 4 ለ 0 በማሸነፍ ወደሚቀጥለው ደረጃ ከሚያልፉት 16 አገራት መካከል አንዷ መሆኗን ስታረጋግጥ፣ የአይቮሪ ኮስት የማለፍ ዕድል በቀጣይ ጨዋታዎች እንዲወሰን ሆኗል።
ብሊንከን ዛሬ ከአይቮሪ ኮስት ፕሬዝደንት አላሳን ዋታራ ጋር እንደሚገናኙ ሲጠበቅ፣ ቀጥሎም ከአፍሪካ ልማት ባንክ ፕሬዝደንት አኪኑዉሚ አዲሲና ጋር በአንድ ቀጠናዊ የሩዝ ምርምር ተቋም ውስጥ እንደሚገናኙ ቀጠሮ መያዙ ተመልክቷል።
ብሊንኪን ጉብኝታቸውን በመቀጠል ወደ ናይጄሪያና አንጎላ እንደሚያቀኑም ይጠበቃል።