"ዩክሬንን መርዳታችንን አናቆምም" ፕሬዚደንት ባይደን

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን

በተቃረበው ምርጫ ዋዜማ በጀርመን የመሰናበቻ ጉብኝት የጀመሩት የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት አባል ሀገሮች ከሩሲያ ጋር ጦርነት ላይ ያለችውን ዩክሬይንን መርዳታቸውን መቀጠል እንዳለባቸው አሳሰቡ።

ዩክሬይን ውጊያው ውስጥ ከገባች ሦስተኛ የክረምት ወቅት ልትይያዝ እየተቃረበች ከመሆኑም ሌላ በምስራቅ ግዛቷ ሽንፈት እያስተናገደች መሆኑ ተጠቁሟል። በዩናይትድ ስቴትሱ ምርጫ ዶናልድ ትረምፕ በድጋሚ ቢመረጡ "ዩክሬን ከዩናይትድ ስቴትስ የምታገኘው ወታደራዊ ድጋፍ ይቀነሳል" በሚል ኪቭ እና አጋሮቿ ሥጋት አድሮባቸዋል።

"ከባድ የክረምት ወቅት እየመጣ ነው" ያሉት ፕሬዚደንት ባይደን "ዩክሬይን ዘላቂ ሰላሟን እስከምታገኝ ድጋፋችንን ልናቋርጥ አንችልም" ብለዋል።

ለዩናይትድ ስቴትሱ ፕሬዚደንት ታላቅ አቀባበል ያደረጉላቸው የጀርመን ፕሬዚደንት ፍራንክ ዋልተር ስታይንሚየር ለሀገሮቻቸው የሁለትዮሽ ግንኙነት እና ለአትላንቲክ ተሻጋሪ ትስስሮች ስለተጫወቱት የመሪነት ሚና ከፍተኛውን የጀርመን የክብር ኒሻን ሸልመዋቸዋል።