የአንጎላ ተቃዋሚ የረሃብ አድማውን አቋረጠ

በአነጎላ የረሃብ አድማ ሲያደርግ የሰነበተው ታዋቂ የራፕ ድምፃዊና (rapper) የፖለቲካ ታጋይ፣ ልዋቲ ቢራዎ (Luaty Beirao) ከ36 ቀናት በኃላ አድማውን አቋርጧል። የራብ አድማውን ለማቆም ቤተሰቦቹና ጓደኞቹ ለጤናው ሰግተው ያቀረቡት ተማፅኖ እንደሆነ ተጠቅሷል።

ለ36 ቀናት በአነጎላ የረሃብ አድማ ሲያደርግ የሰነበተው የራፕ ሙዚቀኛ (rapper)ና የፖለቲካ ታጋይ፣ ልዋቲ ቢራዎ (Luaty Beirao) በትናንትናው ማክሰኞ እለት አድማውን አብቅቷል። ባለቤቱ፣ ቤተሰቦቹና አብረው በእስር ቤት የሚገኙ ጓደኞቹ ለጤናው ሰግተው ባቀረቡት ተማፅኖ አድማውን እንዳቋረጠ ተገልጿል። ቤተሰብና ጠበቃው ልዊስ ናሲመንቶ (Luis Nascimento) በዜናው የተሰማውን ደስታ ሲገልጹ “ድል ይሰማኛል” ብለዋል።

ቢራዎ ከሎሎች 14 የሚሆኑ በአንጎላ ለሰብአዊ መብቶች ከሚሟገቱ የፖለቲካ ታጋዮች ጋር እስከዛሬ በእስር ቤት እንደሚገኝ ታውቋል። ተሟጋቾቹ በመጻሕፍት ክለብ አባልነት ተሰብስበው እያሉ እንደታሰሩ አይዘነጋም። የቀረቡባቸው ክሶች የመንግስቱን ተቋማትን ተመሳጥረው ለማጥቃት ያልማሉ የሚሉ ናቸው።

ቢራዎ አድማውን ሲጀምር የአንጎላ ባለስልጣናት የፖለቲካ ታጋዮቹን ከእስር ቤት እንዲፈትዋቸው ጥሪ ለማቅረብ ነው። በዚህም መሰረት አቤቱታቸው ፍርድ ቤት ቀርቦ ምርመራ እስከሚጀምር መታሰር እንደሌለባቸው አስተውቀዋል። የአንጎላ ፍርድ ቤት የቢራዎን ጉዳይ በሚመለከት ችሎት ሕዳር አጋማሽ ላይ ቀጠሮ ተሰጥቷል። ባለፈው ሰኔ 16 የሚሆኑ የፖለቲካ ታጋዮች የ ሆዜ ኤድዋርዶ ዶስ ሳንቶስን (Jose Eduardo dos Santos) መንግስት ለመገልበጥ አስበዋል በሚል ክስ እደታሰሩ ይታወሳል።

የአሜሪካ ድምጽ ጋዜጠኞች ሪኪ ሽህርዮክ (Ricci Shryock)ና ማሪያማ ዲያሎ (Mariama Diallo) በኢንድያና ዩኒቨርስቲ (Indiana University) የአፍሪቃ ታሪክ ባለሞያ መሊሳ ሞራን (Melissa Mooran)ን እና የደቡብ አፍሪቃ ዓለምአቀፍ እምነስቲ ክልል ቢሮ ማርያና አብረኡ (Mariana Abreu) አነጋግረው የላኩትን ዘገባ ሳሌም ሰለሞን አቅርባዋለች። ከተያያዘው የድምፅ ፋይል በመጫን ያዳምጡ።

Your browser doesn’t support HTML5

የአንጎላ ተቃዋሚ የረሃብ አድማውን አቋረጠ