አማራ ክልል ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መግለጫ ምላሽ ሰጠ

Your browser doesn’t support HTML5

አማራ ክልል ለትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መግለጫ ምላሽ ሰጠ

የአማራ ክልል መንግሥት፣ ባለፈው ሰኞ፣ በክልሉ የመማሪያ መጻሕፍት ላይ የታተመውን ካርታ በተመለከተ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ላወጣው ማስጠንቀቂያ ምላሽ ሰጠ።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ካቢኔ፣ ሁለቱ ክልሎች በይገባኛል የሚወዛገቡባቸውን አካባቢዎች ወደ አማራ ክልል ያካተተ ካርታ በመማሪያ መጻሕፍቱ ላይ መታተሙን በተመለከተ መግለጫ አውጥቶ ነበር። የአማራ ክልል በአስቸኳይ ማስተካከያ እንዲያደርግም አስጠንቅቋል።

አማራ ክልል፣ ዛሬ ኀሙስ ባወጣው ምላሽ ደግሞ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ካቢኔ መግለጫ፣ የአካባቢዎቹን ሕዝቦች ታሪክ፣ ተጨባጭ መረጃንና ነባራዊ ሐቅን የካደ ነው፤ ሲል ተቃውሟል።

SEE ALSO: በአማራ ክልል ለማስተማሪያ በዋለ የመማሪያ መጽሐፍ ላይ ቅሬታ ቀረበ

መግለጫው አያይዞም፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ በተወሰኑ የአማራ ክልል አካባቢዎች ላይ ትንኮሳ እየፈጸመ ስለመኾኑ ጠቅሷል።

በተመሳሳይ፣ የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ/አብን/ ፓርቲ፣ ከትላንት በስቲያ ባወጣው መግለጫ፣ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር፣ የፕሪቶርያውን የሰላም ስምምነት በግልጽ እየጣሰ “የሰላም ስምምነቱ ይከበር፤” ማለቱን “የምጸት ፕሮፓጋንዳ እና የጦርነት ጉሰማ” ሲል አጣጥሏል፡፡

የአላማጣ ከተማ ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ፣ ከትግራይ ክልል ተነሡ ያላቸው የታጠቁ ኀይሎች፣ ዛሬም ተጨማሪ ቦታዎችን በወረራ ይዘዋል፤ ሲል ከሷል፡፡

ከአሜሪካ ድምፅ ጋራ ትላንት ረቡዕ ቆይታ ያደረጉት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር መንግሥት ኮምዩኒኬሽን ጽ/ቤት ኃላፊ ረዳኢ ኃለፎም፣ አስተዳደራቸው የፈጸመው ወረራም ኾነ በወረራ የያዛቸው አካባቢዎች እንደሌሉ ገልጸው አስተባብለዋል፡፡ ዝርዝሩን ከተያያዘው ፋይል ይከታተሉ።