የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነትም ኾነ የፌደራሉ መንግሥት “አከራካሪ” በሚላቸው፣ የማንነት እና የወሰን ጥያቄ ከሚነሣባቸው አካባቢዎች አንዱ በኾነው የራያ አካባቢ፣ መሠረታዊ አገልግሎቶች መቋረጣቸውን፣ የአላማጣ ከተማ አስተዳደር አስታወቀ፡፡
የአላማጣ ከተማ ሆስፒታል፣ ላለፈው አንድ ወር ገደማ አገልግሎት መስጠት በማቋረጡ በሕክምና አገልግሎት ዕጦት የ11 ሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ የከተማዋ ከንቲባ አቶ ኀይሉ አበራ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል፡፡ ሕይወታቸውን ካጡት ውስጥ፣ “ስምንቱ ጨቅላ ሕፃናት ሦስቱ ደግሞ እናቶች ናቸው፤” ብለዋል፡፡
SEE ALSO: ለትግራይ ክልል የ“አከራካሪ” አዋሳኝ አካባቢዎች መግለጫ የአስተዳደሮቹ ምላሽከንቲባው፣ የማንነት እና ራስን በራስ የማስተዳደር ጥያቄ በሚነሣባቸው በአላማጣ ከተማ፣ በራያ አላማጣ፣ ራያ ባላ እና ኮረም አካባቢዎች በሚገኙ 123 ትምህርት ቤቶች ውስጥ የሚማሩ ከ42 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ትምህርታቸውን ለማቋረጥ መገደዳቸውን አስረድተዋል፡፡
ከተማሪዎቹ መካከል፣ ዘንድሮ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ መልቀቂያ ፈተናን የሚወስዱ ከ900 በላይ ተማሪዎችን ግን፣ የወልዲያ ዩኒቨርሲቲ፥ የትምህርት፣ የምግብ እና የማደሪያ አገልግሎቶችን ለመስጠት፣ ከዛሬ ጀምሮ ተማሪዎቹን መቀበል መጀመሩን ዩኒቨርሲቲው አመልክቷል፡፡
በሌላ በኩል ባለፈው ሚያዚያ 8/2016 ዓ.ም ለመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ርዕሰ መስተዳደር ሌተና ጄኔራል ታደሰ ወረደ በአማራ ክልል በተዋቀሩት የራያ አላማጣ ታጣቂዎችና በተፈናቀሉ የትግራይ ሚኒሻዎች መካከል የተቀሰቀሰው የአካባቢ ግጭት ተስፋፍቶ አላማጣ ጫፍ መድረሱን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
SEE ALSO: የአፍሪካ ኅብረት በሰሜን ኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ ጥሪ አቀረበአወዛጋቢ ወይም አጨቃጫቂ እየተባሉ የሚጠሩ አካባቢዎችን በተመለከተም ሌተና ጄነራል ታደሰ ሰሞኑን መቀሌ ላይ በሰጡት ጋዜጣዊ “አካባቢዎቹ የሚታወቁ የትግራይ ይዞታ ናቸው፤ አከራካሪ አይደሉም” ማለታቸውን መዘገባችን ይታወሳል።
ከትግራይ ክልል ኮምዩኒኬሽን ቢሮም ኾነ ከደቡባዊ ትግራይ ዞን፣ ከአማራ ክልል እና ከፌደራል መንግሥት ተጨማሪ መረጃዎችንና አስተያየቶችን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡