በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአፍሪካ ኅብረት በሰሜን ኢትዮጵያ ያሉ ግጭቶች እንዲቆሙ ጥሪ አቀረበ


ፎቶ ፋይል፦ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር የሆኑት ሙሳ ፋኪ ማሃማት
ፎቶ ፋይል፦ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር የሆኑት ሙሳ ፋኪ ማሃማት

በሰሜን ኢትዮጵያ በይገባኛልነት አጨቃጫቂ በሆኑ ሥፍራዎች በሚገኙ ማኅበረሰቦች መካከል እያየለ የመጣው ውጥረት እንዳሳሰበው የአፍሪካ ኅብረት ዛሬ አስታውቋል።

ኅብረቱ፣ ሁሉም ወገኖች ግጭቶችን በአስቸኳይ እንዲያቆሙም ጠይቋል። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው፣ በትግራይና በአማራ ክልሎች መካከል በይገባኛልነት በሚያጨቃጭቁት በአላማጣ ከተማ፣ በራያ አላማጣ፣ ዛታ እና ኦፍላ በዚህ ወር በተከሰቱ ግጭቶች ሳቢያ 50ሺሕ ሰዎች ተፈናቅለዋል።

“በድጋሚ የተፈናቀሉትንና በአካባቢው የሚኖሩ ሲቪሎች ደህንነት ለማረጋገጥ ሁለቱም ወገኖች በአስቸኳይ ግጭቶችን ያቁሙ” ሲሉ የአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር የሆኑት ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጠይቀዋል።

በአጨቃጫቂ ቦታዎቹ ያሉትን ችግሮች ለመፍታት፣ ዋና የመፍትሄ መንገድ ነው ያሉት የፖለቲካ ውይይት መልሶ እንዲጀመርም ኮሚሽነሩ ጠይቀዋል።

በሰሜን ኢትዮጵያ በመንግስት እና በትግራይ ኃይሎች መካከል በነበረው የሁለት ዓመታት ጦርነት፣ ከፌዴራል ጦር ጎን ተሰልፈው የተዋጉት የአማራ ኃይሎች ራያ አላማጣን እንደያዙ፣ በጥቅምት 2014 ፕሪቶሪያ ላይ በተፈረመው የሰላም ስምምነት መሠረትም የአማራ ኃይሎች ከራያ አላማጣ መውጣት እንደነበረባቸው የኤኤፍፒ ዘገባ አመልክቷል።

“የማንነት ጥያቄ ይነሳባቸዋል” ብሎ በገለጸው በራያ አላማጣ እና ሌሎችም ሥፍራዎች ላይ የሕዝባዊ ወያኔ አርነት ትግራይ (ህወሃት) “ወረራ” ፈጽሟል ሲል የአማራ ክልል መስተዳደር ባለፈው ሳምንት ክስ አሰምቷል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት የሆኑት ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው “በአካባቢዎቹ በቅርቡ የሚታዩት ክስተቶች፣ በስፍራዎቹ የሚታዩትን ወይም ይኖራሉ ተብለው የሚታሰቡትን ልዩነቶች በመጠቀም፣ የፕሪቶሪያውን ስምምነት ለማጨናገፍ፣” እርሳቸው “የፕሪቶሪያ ስምምነት ጠላቶች” ብለው የገለጿቸው “ወገኖች ሥራ ነው” ሲሉ በX ማኅበራዊ መድረክ ላይ ባለፈው ሳምንት መልዕክታቸውን አስፍረዋል።

በአካባቢው የሚታዩ ግጭቶችን በተመለከት የሚወጡ ሪፖርቶች፣ የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ እንዳሳሰቡና አሜሪካ፣ ጃፓን፣ እንግሊዝ እና ፈረንሣይ ግጭቱ እንዲረግብ፣ ሲቪሎች ከለላ እንዲያገኙ እና ውይይት እንዲደረግ ጥሪ ማስተላለፋቸውን የኤኤፍፒ ዘገባ አስታውሷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG