የአፍሪካ ልማት ባንክ፤ የፀጥታ ኃይሎች በባንኩ ሠራተኞች ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በሚል ከአንድ ወር በፊት ከኢትዮጵያ ያስወጣቸውን ሰራተኞች እንደሚመልስ አስታውቋል።
ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት የደህንነት ዋስትና በመሰጠቱ፣ ባንኩ በአገሪቱ መደበኛ ሥራውን እንደሚቀጥል፣ ከባንኩ ያወጣውን መግለጫ ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
የባንኩ ፕሬዝደንት አኪኑሚ አዴሲና ከኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ጋር ባለፈው የፈረንጆች ወር መጨረሻ ላይ መነጋገራቸውን እና ጠቅላይ ሚኒስትሩም ለባንኩ ይቅርታ መጠየቃቸውን መግለጫው አመልክቷል።
ከዚህ በተጨማሪም፣ ወደ ባንኩ መተላለፍ የነበረበት እና ጠፍቷል የተባለውን ገንዘብ በተመለከተ ምርመራ ለማድረግ የኢትዮጵያ መንግሥት ለመተባበር እንደተስማማ መግለጫው አመልክቷል።
SEE ALSO: የአፍሪካ ልማት ባንክ ዓለም አቀፍ ሠራተኞቹን በሙሉ “በአስቸኳይ” ከኢትዮጵያ እንደሚያሰወጣ አስታወቀባንኩ በጉዳዩ ላይ አስተያየት ሲሰጥ የመጀመሪያው ሲሆን፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ተፈጠረዋል ስለተባሉት ችግሮች እስከ አሁን ያለው የለም።
“በባንኩ ፕሬዝደንት እና በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ መካከል የነበረውን ውጤታማ ውይይት እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይቅርታ በመጠየቃቸው፣ ባንኩ በኢትዮጵያ የተለመደ ሥራዉን ለመቀጠል ወስኗል” ብሏል የባንኩ መግለጫ።
“ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ለመቻል በምታደርገው ጥረት ባንኩ አስፈላጊ አጋር ነው” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ በ X ማኀበራዊ መድረክ ላይ አስፍረዋል።