ህንድ 368,147 አዲስ የኮሮናቫይረስ ተያዦች መዘገበች

  • ቪኦኤ ዜና
ኮቪድ-19 ህንድ

ኮቪድ-19 ህንድ

ዛሬ ሰኞ ህንድ ውስጥ 368,147 አዲስ የኮሮናቫይረስ ተያዦች መመዝገባቸው ተገለጸ። በየቀኑ ከ300,000 በላይ አዲስ የቫይረሱ ተያዥች ሲገኙ ዛሬ አስራ ሁለተኛው ቀን መሆኑ ነው።

ከዓለም የሚበዛው የኮቪድ-19 ክትባት የሚያመርተው “ዘ ሴረም ኢኒስትቲዩት” የተባለው የመድሃኒት አምራች ተቋም የሚገኘው ህንድ ውስጥ ሆኖ ሳለ ከ1 ነጥብ ሦስት ቢሊዮኑ ህዝቧ የተከተበው ሁለት ከመቶው ብቻ መሆኑ ታውቋል።

የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አዳር ፑንዋላ ለእንግሊዙ ሰንዴይ ታይምስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ

"ወረርሽኙ በዚህ ደረጃ ከባድ እንደሚሆን እግዚአብሄር ራሱም ሊተነብየው የሚችለው አይመስለኝም" ብለዋል።

ኮቪድ-19 ህንድ ውስጥ


የአርባ ዓመቱ ቢሊዮነር ከበርቴው የተቁዋሙ ሥራ አስፈጻሚ በቃለ መጠይቁ በተናገሩት ከባድ ነቀፋ ከቀረበባቸው በኋላ የክትባቱን ዋጋ እንደሚቀንሱ አስታውቀዋል። ያ ሲሆን ሀገሮች ተጨማሪ ክትባት ለማግኘት እና ብዙ ህይወት ለማትረፍ ይችላሉ ሲሉ ተናግረዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ጽህፈት ቤት ሹም ሮን ክሌይን ለሲቢኤስ ቴሌቭዥን በሰጡት ቃል

"ለህንድ በጥድፊያ እርዳታ በመላክ ላይ ነን" ብለዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ያን እያደረገችም ቫይረሱ እንዳይስፋፋ ለመከላከል ርምጃዎች በመውሰድ ላይ መሆኗን አስረድተዋል። ዩናይትድ ስቴትስ ከነገ ማክሰኞ ጀምሮ ከህንድ በረራዎች እንደማታስገባ ባለፈው ዐርብ ዋይት ሃውስ አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ አውስትራሊያ ከህንድ በረራ እንዳይገባ ከልክላለች። ወደህንድ ተጉዞ ሲመለሱ የሚገኙ አውስትሬሊያውያን በገንዘብ እና በእስራት ሊቀጡ እንደሚችሉ ተገልጿል።

ኢንዶኔዥያ በበኩሏ ሁለት የተቀየሩ የኮሮናቫይረስ ዝርያዎች ሃገርዋ መግባታቸውን አስታውቃለች። አንደኛው ከደቡብ አፍሪካ ሌላው ከህንድ መሆኑን ነው የገለጸችው። ይህንኑ ተከትሎ የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታ መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከል (ሲዲ) ተጓዥች ወደኢንዶኔዥያ ከመሄድ እንዲቆጠቡ መክሯል። የኮቪድ መከላከያ ክትባት የወሰዱ ሰዎችም ቢሆኑ በልውጦቹ ቫይረሶች ሊያዙ እና ሊያዛምቱ እንደሚችሉ ነው ሲዲሲ ያሳሰበው።