የጎርፍ አደጋ የ158 ሰዎች ህይወት ባጠፋባት ስፓኝ አስከሬን ፍለጋው ቀጥሏል

የጎርፍ አደጋው ከደረሰ በኋላ ተሽከርካሪዎች በጎርፉ ተጠራርገው ይታያሉ፤ ቫሌንሲያ፤ ስፔን

የአደጋ ጊዜ ሰራተኞች 155ቱ ከምስራቃዊ ቫሌንሲያ ግዛት የሆኑበት እና እስካሁን በተረጋገጡ መረጃዎች መሰረት በጠቅላላው የ158 ሰዎችን ሕይወት በቀጠፈው በስፓኝ በደረሰው ከባድ የጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋ በሕንጻ ፍርስራሽ ከተቀበሩ እና ጎርፉ ከወሰዳቸው ተሽከርካሪዎች ውስጥ የአስከሬን ፍለጋ ሥራቸውን ቀጥለዋል።

በዚያች አገር ታሪክ በገዳይነቱ ከሁሉ የከፋው መሆኑ የተነገረለት የተፈጥሮ አደጋ ያስከተለው የውሃ ናዳ ከከመረው ጭቃ እና ፍርስራሽ የሚወጡት አሳዛኝ ዜናዎች አላበቁም። ጎርፉ ያስከተለው ጉዳት ‘ሱናሚ’ በመባል የሚታወቀውን እና የመሬት መንቀጥቀጥን ተከትሎ የሚደርስ እጅግ አደገኛ ማዕበል የሚያስከትለውን አደጋ የሚያስታውስ ነው ተብሏል። በሕይወት የተረፉት የሟች ወዳጅ ዘመዶቻቸውን በአደጋው የተቆራረጠ አካል ለመሰብሰብ አሳዛኝ እጣ መዳረጋቸው ተዘግቧል።

ከሜዲትራኒያን ባህር ዳርቻ ከባርሴሎና በስተደቡብ በሚገኘው ቫሌንሲያ በደርዘን ከሚቆጠሩ መንደሮች እና የመኖሪያ አካባቢዎች ተሽከርካሪዎ አንዳቸው በሌላው ላይ ተነባብረው፣ ከሥራቸው የተነቀሉ

ዛፎች እና የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች ወዳድቀው፤ እንዲሁም የቤት እቃዎች ተከምረው ይታያሉ።

የገቡበት ያልታወቁት ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር እስካሁን በውል ካለመለየቱ ባሻገር፤ የተጎጂዎች ቁጥር እስካሁን ከተነገረውም ሊጨምር እንደሚችል ተገልጧል።