በግጭቶች የተዳከሙ ትምህርት ቤቶች ተፋላሚዎች እንዲወያዩ ተማፀኑ

Your browser doesn’t support HTML5

በግጭቶች የተዳከሙ ትምህርት ቤቶች ተፋላሚዎች እንዲወያዩ ተማፀኑ

ግጭቶች በቀጠሉባቸው የአማራ እና የኦሮሚያ ክልሎች አካባቢዎች የሚገኙ ትምህርት ቤቶች መምህራንና ተማሪዎች፣ የግጭቱ ተሳታፊዎች የሕዝቡን ሥቃይ ከግምት በማስገባት ወደ ውይይት እንዲመጡ ተማፅነዋል፡፡

የአሜሪካ ድምፅ ያነጋገራቸው በግጭቶቹ አካባቢዎች የሚገኙ መምህራንና ተማሪዎች፣ በማያባሩ ውጊያዎች የተነሣ የትምህርት ቤቶቻቸው የመማር ማስተማር ይዞታዎች መዳከማቸውንና የወደሙትንም መልሶ የማቋቋም ሥራው አዳጋች እንደሆነባቸው ገልጸዋል፡፡

ከትምህርት ገበታቸው የሚርቁ ተማሪዎች ቁጥር በየጊዜው እየጨመረ እንደሆነ ጠቁመው፣ ረኀብ እና በትምህርት ሰዓት የሚያንዣብቡ ድሮኖችም፣ “የተማሪውን አካል እና መንፈስ እየጎዱ ናቸው፤” ሲሉ አመልክተዋል፡፡

የመንግሥታቱ ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበርያ ቢሮ ወይም በምኅጻሩ ዩኤን-ኦቻ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ በግጭት እና በአየር ንበረት ለውጥ ሳቢያ 7ነጥብ6 ሚሊዮን ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ርቀው እንደሚገኙ፣ ከአራት ወራት በፊት ባወጣው መረጃ አስታውቋል። ይህ አኀዝም ግጭቶች እስካልቆሙ ድረስ ማሻቀቡን እንደሚቀጥል ይጠበቃል።