በኢትዮጵያ ችግር ያዋለደው ቀዳሚው የዐይነ ስውራን ሙዓለ ሕፃናት የማስፋፊያ ድጋፍን ይሻል

Your browser doesn’t support HTML5

በኢትዮጵያ ችግር ያዋለደው ቀዳሚው የዐይነ ስውራን ሙዓለ ሕፃናት የማስፋፊያ ድጋፍን ይሻል

ያለጊዜያቸው የተወለዱ ልጆቻቸው የዐይን ብርሃናቸውን ያጡባቸውና እክሉ ያገናኛቸው እናቶች፣ አንድ ገባሬ ሠናይ ተቋም ለመመሥረት ሲነሣሡ፣ ከትምህርት ገበታ ርቀው በየቤታቸው የተቀመጡ የችግሩ ተጠቂ ሕፃናት ጥቂቶች እንዳልኾኑ ለመታዘብ ችለዋል፡፡

እነኚኽ እናቶች፣ ልጆቻቸው ለዐቅመ ትምህርት ሲደርሱ፣ እንደ እኩዮቻቸው ወደ ሙዓለ ሕፃናት እንዲገቡ በፈለጉበት ወቅት ተቀባይ ዐጥተው ያጋጠማቸው እንግልት፣ የራሳቸውንም ኾነ የልጆቻቸውን ሕይወት ከባድ እንዳደረገባቸው ይናገራሉ፡፡

በዋና ከተማዋ ዐዲስ አበባ፣ ልጆቻቸውን ለማስመዝገብ በሔዱባቸው ትምህርት ቤቶች በሙሉ፣ ከስምንት ዓመት ዕድሜ በፊት ሊቀበላቸው የሚችል ተቋም አለመኖሩን ያስተዋሉት ሰባት እናቶች ታዲያ፣ “ቪዥን ማየት የተሳናቸው ሕፃናት ወላጆች በጎ አድራጎት ድርጅት” በማለት የመጀመሪያውን ሙዓለ ሕፃናት በ2015 ዓ.ም. ለመክፈት በቅተዋል፡፡

ከተለያዩ ሞያዎች የመጡት እናቶች፣ ከበጎ ፈቃደኞች እና ከግብረ ሠናይ ተቋማት በሚያገኙት ድጋፍ አማካይነት፣ ቤተ በመከራየት የልዩ ፍላጎት መምህራንን ለመቅጠር ችለዋል፡፡ ኾኖም፣ በየቤታቸው የተቀመጡ የእክሉ ተጠቂ ሕፃናት ጥቂት እንዳልኾነ የገለጹት መሥራቾቹ፣ ትምህርት ቤቱን እንደሚፈለገው አስፋፍተው የመቀበል ዐቅም እንደሌላቸው፣ ለአሜሪካ ድምፅ አስታውቀዋል።

ኤደን ገረመው ከመሥራቾቹ መካከል ሁለቱን አነጋግራለች።