ከኻርቱም መውጣት የተሳናቸው ስደተኞች ዓለም አቀፍ ተቋማትን እየተማፀኑ ነው

Your browser doesn’t support HTML5

ከኻርቱም መውጣት የተሳናቸው ስደተኞች ዓለም አቀፍ ተቋማትን እየተማፀኑ ነው

በሱዳን የጦር ኃይል እና በፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ልዩ ኃይል መካከል የሚደረገውን ውጊያ ሸሽተው የሚወጡ ስደተኞች፣ ከካርቱም ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ለመድረስ፣ 150ሺሕ የሱዳን ፓውንድ ወይም እስከ 14ሺሕ የኢትዮጵያ ብር እንደሚጠየቁ ገለጹ። ገንዘቡን ከፍለው መውጣት ያልቻሉ ስደተኞችም፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እንዲታደጓቸው ጠይቀዋል።

መብራት፣ ውኃ እና የኢንተርኔት አገልግሎት፣ በኻርቱም እና አካባቢዋ መቋረጡን ስደተኞቹ ይናገራሉ፤ በጸጥታ ስጋት ምክንያትም፣ በከተማዋ እንቅስቃሴ ማድረግ እንደማይቻል ይገልጻሉ፤ የነዳጅ ዋጋም በከፍተኛ መጠን መናሩን ያመለክታሉ። ውጊያውን ሸሽተው ከኻርቱም ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ለመድረስ የሚፈልጉ ስደተኞችም፣ 150ሺሕ የሱዳን ፓውንድ ወይም እስከ 14 ሺሕ የኢትዮጵያ ብር እንደሚጠየቁ ያማርራሉ።

ወደ ኢትዮጵያ ድንበር ለመድረስ የትራንስፖርት ዋጋ በመወደዱና በመንገዶች ላይም የጸጥታ ስጋት በመኖሩ፣ የሚላስ የሚቀመስ ለማግኘት በሚቸግርበት ካርቱም ኹኔታዎች በዚኽ ከቀጠሉ፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ የሚበሉትን ሊያጡ እንደሚችሉ በካርቱም በስደት የሚኖሩት አቶ ብርሃነ ማርያም ተሰማ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

ሮዛ ከድር፣ በኻርቱም የምትኖር ስደተኛ ስትኾን፣ በዐቅም ማነስ ምክንያት ከተማዋን ለቀው ለመውጣት አለመቻላቸውን በመጥቀስ፣ በአሁን ሰዓት ኻርቱም አስፈሪ ድባብ መላበሱዋን ትናገራለች።

ሌላዋ በኻርቱም በቤት ሠራተኝነት ታገልግል የነበረችውና የሁለት ልጆች እናት የኾነችው ዘቢባ ዩሱፍም፣ ከተማዋን ለቆ ለመሔድ ምንም ዓይነት ዐቅም እንደሌላት በመግለጽ፣ ዓለም አቀፍ ተቋማት እጃቸውን እንዲዘረጉላቸው ጠይቃለች።

ኻርቱም አሁን ባለችበት የጸጥታ መታወክም ኾነ የመሠረተ ልማት መቆራረጥ፣ ለኑሮ የምትመች አይደለችም። ስደተኞቹም፣ ሊረዳቸው የሞከረ የመንግሥትም ኾነ የዓለም አቀፍ ተቋም አለመኖሩን፣ ለአሜሪካ ድምፅ አስታውቀዋል። በኻርቱም፣ በቀን ሠራተኝነት የሚሠራው ተሰማ ሀንድሶ፣ በአሁን ሰዓት የሚሻው ነገር ቢኖር፣ ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ብቻ እንደኾነ ይናገራል።

ወደ ኢትዮጵያ መመለስ ግን፣ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ምርጫ አይደለም፡፡ በፖለቲካ ጥገኝነት ላይ የሚገኙት አቶ ብርሃነ ማርያም ተሰማ፣ ምንም እንኳን ከአምስት ቤተሰቦቻቸው ጋራ ኻርቱምን ለቅቆ ለመሔድ የሚያስችል ዐቅም ባይኖራቸውም፤ የመንግሥታቱ ድርጅትን የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ድጋፍ መጠበቅን ምርጫቸው አድርገዋል።

በሱዳን፣ ዋና ከተማዪቱን ኻርቱምን ጨምሮ፣ በልዩ ልዩ የአገሪቱ ክፍል ያሉ ስደተኞች፣ ዓለም አቀፍ ገባሬ ሠናይ ተቋማት ፊታቸውን እንዲያዞሩላቸው እየተማፀኑ ይገኛሉ።

በአንጻሩ የአሜሪካ ድምፅ፣ በኻርቱም የሚገኘውን የመንግሥታቱ ድርጅት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነርን በስልክ ለማነጋገር ተደጋጋሚ ሙከራ ቢያደርግም ለጊዜው አልተሳካም።

ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ፊሊፖ ግራንዲ፣ ከትላንት በስቲያ በአወጡት መግለጫ፣ በዐሥር ሺሕዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች፣ በጸጥታ ምክንያት አገራቸውን ለቀው በመውጣት ላይ እንደኾኑ ገልጸዋል፡፡ በአሁን ሰዓት በሱዳን፣ 3ነጥብ7 ሚሊየን የሚኾኑ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች እንዳሉና ይህ አኀዝም እየጨመረ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።

ኮሚሽነሩ አክለውም፣ ድርጅታቸው፣ በጸጥታ ምክንያት ሥራውን በተገቢው መንገድ ለማከናወን እክል እንደገጠመው በመጥቀስ፣ ለሁለቱ ተፋላሚ ኃይሎች የሰላም ጥሪ አድርገዋል።