የሱዳኑ ተኩስ የማቆም ስምምነትና የቀጠለው ሲቪሎችን የመታደግ ተልእኮ

Your browser doesn’t support HTML5

“ሕይወት አድን” በተባለው የሱዳኑ የተኩስ ማቆም ስምምነት የቀጠለው ዜጎችን የመታደግ ተልእኮ

ላለፉት 48 ሰዓታት ከተደረገ ከፍተኛ ድርድር በኋላ፣ የሱዳን የጦር ኃይል እና ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ልዩ ኃይል፣ ከሰኞ እኩለ ሌሊት ጀምሮ ቢያንስ ለ72 ሰዓታት፣ ሀገር አቀፍ የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ መስማማታቸውን፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን ቢያስታውቁም፣ የውጭ መንግሥታት ዲፕሎማቶቻቸውንና ዜጎቻቸውን ከሱዳን ማውጣቱን ቀጥለዋል።

“በድፍረት እና ሞያዊ ብቃት” የተከናወነ ተልእኮ
በጦርነት ከምትታመሰው የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም፣ 700 ሰዎችን የጫኑ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መኪናዎች፣ 850 ኪሎ ሜትር የሚፈጀውን አደገኛ ጉዞ አልፈው፣ በቀይ ባሕር ዳርቻ ወደምትገኘው ፖርት ሱዳን ደርሰዋል።
ባለፈው ቅዳሜም፣ የአሜሪካ ጦር ሦስት ሄሊኮፕተሮችን ልኮ የአሜሪካ ኤምባሲ ሠራተኞችን ከካርቱም ማውጣት በመቻሉ፣ የዋይት ሓውስ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ ጃክ ሱሊቫን ምስጋናቸውን ገልጸዋል።

“በድፍረት እና በሞያዊ ብቃት ተግባራቸውን በአከናወኑ የኤምባሲያችን ሠራተኞች ኩራት ይሰማናል። በተሳካ ኹኔታ እነርሱን ደኅንነታቸው ወደሚጠበቅበት ስፍራ ለወሰዷቸው የጸጥታ አባሎቻችን ተወዳዳሪ የሌለው ችሎታም እናመሰግናለን።ጅቡቲ፣ ኢትዮጵያ እና ሳዑዲ አረቢያም፣ እያንዳንዳቸው ለስኬታችን ወሳኝ ስለነበሩ እናመሰግናቸዋለን፤” ብለዋል።

በአሁኑ ሰዓት ምን ያክል አሜሪካውያን ሱዳን ውስጥ እንደቀሩና ከሀገር ለመውጣት ምን ዐይነት አማራጮች እንዳላቸው፣ በአሜሪካ ድምፅ ጥያቄ የቀረበላቸው የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን፣ በሱዳን የሚገኙ አሜሪካውያን ትክክለኛው ቁጥር እንደሌላቸው ጠቅሰው፣ የአሜሪካ ዜጎች በሌሎች ሀገራት የተዘጋጁ መኪናዎችን እንዲጋሩ ለማድረግ እየተሞከረ መኾኑን አመልክተዋል።

አያይዘውም “ምን ያህል አሜሪካውያን፥ ከእኛ ጋራ ወይም ከእኛ ጋራ ግንኙነት ካላቸው አካላት ጋር እንደተመዘገቡ አናውቅም፤ ነገር ግን በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎች ከሱዳን ለመልቀቅ ፍላጎታቸውን ገልጸዋል።” ብለዋል።

የሱዳን የጦር ኃይል እና ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ልዩ ኃይል የሚያድርጉትን ውጊያ ሸሽተው ለመሰደድ የተዘጋጁ ዜጎች ካርቱም ውስጥ/ ሚያዝያ 16/2015 ዓ.ም

በተመሳሳይ፣ ከሱዳን የተፈናቀሉ 189 ሰዎችን የያዘ የሳዑዲ አረብያ የባሕር ኃይል፣ ጂዳ በሚገኘው የንጉሥ ፋይሰል ወደብ ላይ ማረፉን፣ የአካባቢው ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። ከእነዚህ ውስጥ ዐሥሮቹ፣ የሳዑዲ አረቢያ ዜግነት ያላቸው ሲኾኑ፣ የተቀሩት ግን የልዩ ልዩ ሀገራት ዜጎች ናቸው። ሰዎቹን ያጓጓዙት የጦር ኃይል አባላት፣ ሕፃናትንና አዛውንትን ወደ ወደብ በማውረድ የረዷቸው ሲኾን፣ አንዳንዶቹ ተጓዦች የሳዑዲ አረቢያን ባንዲራ ሲያውለበልቡ ታይተዋል።
ዜጎቻቸውን ከሱዳን ለማስወጣት እየጣሩ ያሉት አብዛኞቹ ሀገራት፣ ወታደራዊ የአየር ማመላለሻዎችን የሚጠቀሙ ሲኾን፣ ፈረንሳይ፥ ጎረቤት ሀገር በኾነችው ጅቡቲ የሚገኘውን ወታደራዊ የአየር ማረፊያ ተጠቅማለች።
ይህም ሁሉ ኾኖ ግን፣ ዜጎችን የማስወጣቱ ሒደት ቀላል አይደለም። አሁንም፣ ወደ 2ሺሕ የሚጠጉ የእንግሊዝ ዜግነት ያላቸው ሰዎች በሱዳን ይገኛሉ፡፡ አብዛኞቹ መንግሥታቸው መውጣት ስለሚችሉበት መንገድ በቂ መረጃ እየሰጣቸው አለመኾኑን በመግለጽ ያማርራሉ።

“ሱዳንን ከጥልቁ አፋፍ እንመልሳት”
ሀገራት ዜጎቻቸውን ለማስወጣት እየተረባረቡ ባሉበት በዚኽ ወቅት፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ፣ ባለፈው ሰኞ በሰጡት መግለጫ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ከሱዳን ለቆ እንደማይወጣ አስታውቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ የሱዳንን ወቅታዊ ኹኔታ በተመለከተ ሐሙስ ሚያዝያ 12/2015 ዓ.ም ኒዮርክ ውስጥ ለጋዜጠኞች

“በግልጽ ልናገር፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ከሱዳን እየወጣ አይደለም። የእኛ ተልእኮ፣ የሱዳን ሕዝብ ወደፊት ሰላሙ እና ደኅንነቱ የተጠበቀ እንዲኾን ያለውን ምኞት መደገፍ ነው፤” ብለዋል ጉተሬዥ፡፡ አያይዘውም፣ “በዚኽ አስቸጋሪ ወቅት፣ ከእነርሱ ጋራ እንቆማለን። አንዳንድ የድርጅቱ ሠራተኞች እና ቤተሰቦች፣ በጊዜያዊነት በሱዳንም ኾነ ከሱዳን ውጪ ወደሚገኝ ቦታ እንዲሔዱ ፈቅጃለኹ። ነገር ግን ኹሉም የጸጥታው ምክር ቤት አባላት፥ ግጭቱ እንዲቆም፣ ሥርዐት ወደነበረበት እንዲመለስና ወደ ዴሞክራሲያዊ የሽግግር መንገድ እንዲገባ በኹሉም ወገኖች ላይ ከፍተኛ ግፊት እንዲያደርጉ እጠይቃለኹ። ኹላችንም ያለንን ኃይል ተጠቅመን፣ ሱዳንን ከጥልቁ አፋፍ መመለስ አለብን፤” ብለዋል።
የውጭ ሀገራት ዜጎቻቸውን አስወጥተው ካጠናቀቁ፣ “የሁለቱ ጀነራሎች ኃይሎች የሚያደርጉት ውጊያ ሊያይል ይችላል፤” የሚል ስጋት እየተጠናከረ መጥቷል። በመኾኑም፣ በርካታ ሱዳናውያን፣ ሀገራቸውን እያመሰ ካለው ግጭት ለማምለጥ መንገድ እየፈለጉ ናቸው። ጉተሬዥ በመግለጫቸው፣ ሁለቱ ተዋጊ ቡድኖች የጤና አገልግሎት መስጫ ተቋማትን ጨምሮ ሲቪሎች በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ላይ የሚያደርጉትን የአየር ድብደባና ጥቃት አውግዘው፣ ውጊያው እንዲቆምና ያልተገደበ ሰብአዊ ርዳታ ለሕዝቡ እንዲደርስ ጥሪ አቅርበዋል።
ውጊያው አሁን ባለበት ደረጃ ላይ ካልተገታ፣ ቀጣናዊ መዘዙ የከፋ እንደኾነ ጉተሬዥ ሲያስረዱ፣ “በሱዳን ያለው ኹኔታ እየተባባሰ ነው። ግጭቱ እ.አ.አ. ሚያዝያ 15 ቀን ከጀመረ ወዲህ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተገድለዋል፤ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ጉዳት ደርሶባቸዋል። ይህ ውጊያ ማብቃት አለበት። አለበለዚያ በሱዳን ውስጥ ብቻ ሳይኾን፣ አጠቃላይ ቀጣናውን ያካተተ አደገኛ መበታተን ያስከትላል፤” ብለዋል፡፡

ወደ ሆስፒታል መድረስ ያልቻሉ ሕሙማን
ሁለቱ የሱዳን ተዋጊዎች በሚያደርጉት ውጊያ፣ አጣብቂኝ ውስጥ በገባችው ካርቱም የሚገኙ ሆስፒታሎችም ትልቅ ቀውስ ላይ ናቸው። በድንገት የተከሠተው ውጊያ፣ ዶክተሮችንና ነርሶችን ከአንዳንድ ሆስፒታሎች ውስጥ መውጣት እንዳይችሉ ሲያደርጋቸው፣ ሌሎችን ደግሞ ወደ ሆስፒታሎች መድረስ እንዳይችሉ አከላክሏቸዋል።
አሕመድ ቃሲም፣ ጦርነቱ ከተጀመረ አንሥቶ እስከ አሁን፣ በ17 የእጥበት ማሽኖች እየታገዘ በመሥራት ላይ የሚገኝ ብቸኛው የኩላሊት እጥበት ማዕከል ሲኾን፣ በተቋም የሚሠሩት ዶክተር ኦትማን ታጅ ኤል-ዴይን፣ “የኩላሊት ሕመምተኞች በየሁለት ቀኑ የኩላሊት እጥበት ማድረግ ይኖርባቸዋል። አሁን ለ10 ቀናት ይህን ያላደረጉ ሕመምተኞች አሉ። ይህን ካላደረጉ፣ ውኃ ወደ ሳምባቸው ስለሚገባ የመሞት ዕድላቸው 80 ከመቶ ይኾናል፤” ሲሉ፣ ወደ ሆስፒታሉ መምጣት ያልቻሉ ሕመምተኞች፣ ሕይወታቸው አደጋ ላይ መኾኑን ይገልጻሉ።

SEE ALSO: በሱዳን ጦርነት ምክንያት የኩላሊት ዕጥበት ህክምና መስተጓጎል ያስጨነቃቸው ህሙማን

“በዚኽ ማዕከል የኩላሊት እጥበት አደርጋለኹ፤ ላለፉት ዘጠኝ ቀናት ግን ማዕከሉ ተዘግቶ ስለነበር መምጣት አልቻልኹም፤” የሚለው፣ የሆስፒታሉ ታካሚ ባቶፍ ሻሪፍ፣ ለቀናት ሕክምናውን ማድረግ አልቻለም ነበር። ወደ ሆስፒታሉ ለመምጣት ለትራንስፖርት 40 ዶላር መክፈል እንዳለበት የሚገልጸው ሻሪፍ፣ “ሰዎች ገንዘብ የላቸውም። ወደ እኛ የሚመጡ ሕመምተኞች፣ ካለፈው ሳምንት ቅዳሜ ጀምሮ አልመጡም። በተለይ ሕመማቸው ከፍተኛ ደረጃ ላይ የደረሰ ሰዎች መቋቋም አይችሉም። ለሰዎች መጓጓዣ መንገዱን ክፍት ማድረግ ነበረባቸው፤ ነገር ግን ምንም የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት የለም፤” ብሏል።

የ72 ሰዓቱ ተኩስ አቁም እንደ “ሕይወት አድን ነው”
የሱዳን ተዋጊዎች፣ ለ72 ሰዓታት የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረሳቸውን፣ ብሊንክን ይፋ ከአደረጉ በኋላ፣ ዓለም አቀፉ የቀይ መስቀል ኮሚቴ በአወጣው መግለጫ፥ ጊዜያዊ የተኩስ ማቆም ስምምነቱ፣ ያለምግብ፣ ንጹሕ ውኃ እና የሕክምና አገልግሎት ከቤታቸው ታፍነው ለመቀመጥ ለተገደዱ ሰላማውያን ሰዎች፣ “ሕይወት አድን” መኾኑን አስታውቋል።
“ካርቱም ሚሊየኖች የሚኖሩባት ከተማ ናት፤” ያሉት የኮሚቴው የአፍሪካ ዲሬክተር ፓትሪክ ዩሱፍ፣ ከባድ ፈንጂዎች ጥቅም ላይ በሚውሉበት ጊዜ፣ ጎዳናዎች የጦር አውድማ እንደሚኾኑና ዜጎችም ከፍተኛ ዋጋ እንደሚከፍሉ በመግለጽ፣ ዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ዘላቂ ፖለቲካዊ መፍትሔ በማምጣት ደም መፋሰሱን እንዲያስቆም አሳስበዋል።

ዛሬ ማክሰኞ ሚያዝያ 17/2015 ዓ.ም በውጊያው ምክኒያት በፈራረሱ ቤቶች መካከል አንድ ሰው ሲራመድ

የዋግነር ቡድን ጣልቃ ገብቷል?
በሌላ በኩል፣ በሱዳን የታጣቂ ኃይሎች ውጊያ ውስጥ፣ የውጭ ሀገራት ጣልቃ ገብነትን ተጠይቀው ምላሽ የሰጡት የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንክን፣ በተለይ የሩሲያ ቅጥረኛ ተዋጊዎች ስለኾኑት ዋግነር ግሩፕ ሲገልጹ፣ “ዋግነር ቡድን፥ በሱዳን ያለው እንቅስቃሴ ያሳስበናል። እነርሱ ባሉባቸው የአፍሪካ እና ሌሎች ሀገራት በሙሉ፣ የበለጠ ሞት እና ጥፋት ነው የሚመጣው። ስለዚኽ በሱዳንም ተጨማሪ እንቅስቃሴ እንዳይኖራቸው ማድረግ በጣም አስፈላጊ ነው። በርካታ ሀገራት፣ ይህ ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው አውቃለኹ፤” ብለዋል።
በስትራቴጂያዊ ዓለም አቀፍ ጥናቶች ማዕከል የፖለቲካ ተንታኝ የኾኑት ካምሮን ሃድሰን፣ ከአሜሪካ ድምፅ ጋራ በአደረጉት ቃለ ምልልስ፣ የሩሲያ ተቋም የኾነውና በሩሲያ መንግሥት የሚደገፈው ዋግነር ግሩፕ፣ ለሱዳኑ ፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይል(አርኤስኤፍ)፣ የመሣሪያ ድጋፍ እንደሚያደርጉ የሚያሳዩ ሪፖርቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ ይህም ኹኔታውን እንደሚቀይረው ያመለክታሉ።
“የሱዳንን ጦር ለማጥቃት፥ በሰው የሚሠሩ ተንቀሳቃሽ የአየር መቃወሚያዎችን፣ በትከሻ የሚተኮሱ ሮኬቶችን፣ ታንኮችንና መሰል ከባድ ትጥቆችን አቅረበው ሊኾን እንደሚችል እንረዳለን። ይህ እውነት ከኾነና እነዚኽ ነገሮች በውጊያው ላይ ጥቅም ላይ ከዋሉ፣ ኹኔታው ለአር ኤስኤፍ እንዲያጋድል ሊያደርግ ይችላል፡፡”
ሃድሰን አያይዘውም፣ “ግብጽ ደግሞ በግጭቱ የሱዳን ጦር ኃይሎችን በግልጽ ትደግፋለች፤” ይላሉ። ስለ ግብጽ ፍላጎት አክለው ሲናገሩ፣ “የጦር ሠራዊቱ ሀገሪቱን ሲቆጣጠር ለማየት ፍላጎት እንዳላቸው አይሸሽጉም። ኾኖም፣ በተለይ በሲቪል የሚመራ የሽግግር መንግሥት በሱዳን ለማየት ፍላጎት ኖሯቸው አያውቅም፤” ብለዋል፡፡
በሱዳን ያለውን ግጭት በማባባስ፣ በተለይ በመካከለኛው ምሥራቅ አፍሪካ የሚገኙ ሀገራትን የወቀሱት የኬንያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አልፍሬድ ሙቱዋ፣ ዋግነር ቡድንና ሌሎች የውጭ ኃይሎች፣ መሣሪያ ከማቅረብና ግጭቱን ከማባባስ እንዲቆጠቡ ጠይቀዋል።
ኬንያ፣ በሁለቱ ጀነራሎች መካከል የተፈጠረውን ግጭት ለማሸማገል፣ ፈቃደኛ መኾኗን በማሳወቅ፣ በሱዳናውያን ሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ሥቃይ ለማስቆም፣ ከስምምነት ላይ ሊደረስ ይችላል፤ የሚል ተስፋን አሳይተዋል።

/የአሜሪካ ድምፅ ዘጋቢ ሲንዲ ሴይን ያጠናቀረችውን ዘገባ ከአሶሽየትድ ፕሬስ ዘገባዎች ጋር አቀናጅታ ስመኝሽ የቆየ ወደ አማርኛ መልሳዋለች/ጽ.ግ/