ባይደን ደኅና መሆናቸውን ገለፁ

  • ቪኦኤ ዜና
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

ለኮቪድ-19 መጋለጣቸው የተነገረውና የበሽታው ቀላል ምልክቶች እንደሚታዩባቸው የተገለፀው የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ደኅና መሆናቸውንና ሥራቸውን እያከናወኑ መሆናቸውን ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት በቴሌቪዥን በተላለፈ መልዕክት ገልፀዋል።

“ደኅና ነኝ፣ ስለጭንቀታችሁ አመሠግናለሁ፤ ሥራዬን እያከናወንኩ ነኝ” ብለዋል ባይደን ባስተላለፉት አጭር መልዕክት።

ዋይት ሃውስ ውስጥ አሁን እየተሰጠ ባለ ጋዜጣዊ መግለጫ የቤተ መንግሥቱ ቃል አቀባይ ካሪን ዣን-ፒየር ስለፕሬዚዳንቱ ጤንነት ለጋዜጠኞች ሲናገሩ ሃኪሞቻቸው ዛሬ ተከታታይ ምርመራ ሲያደርጉ ለሳርስ-ኮቭ2 ቫይረስ መጋለጣቸውን ማስተዋላቸውንና በኋላም አከታትለው ባደረጉት ምርመራ ማረጋገጣቸውን የሚገልፀውን መግለጫ በንባብ አሰምተዋል።

የዋይት ሃውስ የኮሮናቫይረስ ምላሽ አስተባባሪ ዶ/ር አሺሽ ዣ ከፕሬዚዳንቱና ከሃኪማቸውም ጋር መነጋገራቸውን፣ ፕሬዚዳንቱ ሙሉውን ክትባትና ሁለት ማጠናከሪያዎችን መውሰዳቸውን፣ የሰውነታቸው በሽታን የመቋቋም ሁኔታ አስተማማኝ መሆኑን፣ የሚስተዋሉባቸው እንደ ደረቅ ሳል፣ ቀላል መናፈጥና የድካም ስሜትን የመሳሰሉ “ቀላል” ያሏቸው ምልክቶች መሆናቸውን አመልክተዋል።

የዩናይትድ ስቴትስ የበሽታዎች መቆጣጠሪያና መከላከያ ማዕከላት /ሲዲሲ/ መመሪያ በሚያዝዘው መሠረት ፕሬዚዳንቱ ቤተመንግሥቱ ውስጥ ትነጥለው እንደሚገኙና ሁሉንም ሥራዎቻቸውን በተሟላ መልኩ እየተወጡ እንደሚቆዩ ዶ/ር ዣ ጠቁመው የፓክስሎቪድ ህክምና መጀመራቸውን ገልፀዋል።

ፕሬዚዳንቱ “እጅግ በጣም ጥሩ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ፣ ትናንትም ማሳቹሴትስ ውስጥ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ሙቀት ለግማሽ ሰዓት ያህል በጥሩ ሁኔታ ንግግር ማድረጋቸውን” ቃል አቀባይዋ አስታውሰዋል።

ባለቤታቸው ዶ/ር ጂል ባይደን ከቫይረሱ ነፃ መሆናቸው መረጋገጡንና ለዛሬ በተያዙ ዕቅዶች መሠረት ሥራዎቻቸውን እያከናወኑ መሆናቸውንም ቃል አቀባይዋ ዣን ፒየር ተናገረዋል።

ፕሬዚዳንት ባይደን 79 ዓመታቸው ነው።