በአባ ገዳዎች የሚደረግ የእርቅ ሂደት የወንጀል ተጠያቂነትን ሊያስተጓጉል እንደማይገባ ኢሰመኮ አሳሰበ

Your browser doesn’t support HTML5

በአባ ገዳዎች የሚደረግ የእርቅ ሂደት የወንጀል ተጠያቂነትን ሊያስተጓጉል እንደማይገባ ኢሰመኮ አሳሰበ

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን በከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባላት ግድያን በተመለከተ በአባ ገዳዎች የተጀመረው ሽምግል እና የእርቅ ሂደት፤ “የወንጀል ተጠያቂነትን መተካት ወይም ማስተጓጎል የለበትም” ሲል አሳሰበ።

ጉዳዩን በቅርበት እየተከታተሉ መሆኑን የሚናገሩት የኦሮሞ አባ ገዳዎች ኅብረት ጸሐፊ እና የቱለማ አባ ገዳ ጎበና ሆላ “እርቀ ሰላም በገዳ ሥርዓት መንገድ እንዲወርድ እየተሠራ ነው” ሲሉ ለአሜሪካ ድምፅ ገልጸዋል ።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን የከረዩ የሚችሌ ገዳ የጅላ አባ ገዳዎች ግድያ ላይ ያደረገውን የምርመራ ሪፖርት ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ባደረገበት ወቅት የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት በጅላ አባላቱ ላይ ግድያ የፈጸሙና ያስፈጸሙ አባላት፤ ተገቢ የሆነ የወንጀል ምርመራ ተደርጎ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥ እና ለተጎጂ ቤተሰቦች ተገቢ የሆነ ካሳ እንዲከፈላቸው ምክረ ሐሳብ አቅርቦ የነበረ ሲሆን አሁን በሽምግልናና በእርቅ የተጀመረው ሂደት የወንጀል ተጠያቂነትን እንዳያስተጓጉል ሲል ትናንት ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

በወቅቱ ኮሚሽኑ ያቀረበውን የምርመራ ጥሪ ተከትሎ የኦሮምያ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን ጉዳዩን በመመርመር ተጠያቂነትን ለማረጋገጥ የሚሠራ መሆኑን ጥር 25 ቀን 2014 ዓ.ም. በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ ማሳወቁም የጠቀሰው የኮሚሽኑ መግለጫ ይህንኑ ተከትሎም የተሠሩ ስራዎች ያሉበትን ደረጃ ለመገምገም ከየካቲት 28 እስከ መጋቢት 3 ቀን 2014 ዓ.ም. ክትትል ማድረጉን አስታውቋል፡፡

በክትትሉም የኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ ቢሮ፣ የኦሮምያ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ፖሊስ ኮሚሽን፣ የምሥራቅ ሸዋ ዞን ፖሊስ መምሪያ፣ ግድያውን ለመመርመር የተዋቀረውን የምርመራ ቡድን እንዲሁም የከረዩ ማኅበረሰብ የሀገር ሽማግሌዎችን ባነጋገረበት ወቅት መርማሪ ቡድን ተቋቁሞ ሥራ የጀመረ መሆኑን እንዳረጋገጠ የኮሚሽኑ መግለጫ ይዘረዝራል።

በሂደቱ የተወሰኑ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የገለፀው የኮሚሽኑ ሪፖርት፣

"በአንድ በኩል በአካባቢው ማኅበረሰብ በግድያው ላይ ተሳትፎ ያላቸው መሆኑን የተጠቆሙ፣ አልያም በድርጊቱ ዋነኛ ፈጻሚ ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰዎች ገና በቁጥጥር ስር ያልዋሉ ወይም ምርመራ እየተደረገባቸው አለመሆኑን" ጠቅሷል።

በተለያየ የመንግሥት የሥራ ኃላፊነት ቦታዎች ላይ የሚገኙ ሰዎችም ተጠርጣሪዎች መሆናቸውን የጠቆመው የኮሚሽኑ መግለጫ ይህ ሁኔታ የምርመራ ሂደቱን ማደናቀፉና በእስር ላይ ያሉትም ቢሆኑ እስካሁን ፍርድ ቤት አለመቅረባቸውን ኮሚሽኑ በመግለጫው አስፍሯል።

በክልሉ መንግሥት እና በከረዩ ማኅበረሰብ የሀገር ሽማግሌዎች መካከል ሽምግልና እየተካሄደ መሆኑን የገለፁት የኮሚሽኑ የአካባቢያዊ ዳይሬክቶሬት የክትትልና ምርመራ ሥራ ክፍል ሀላፊ አቶ ኢማድ አብዱልፈታ ለአሜሪካ ድምፅ የተቋማቸውን አቋም ገልጸዋል።