መንግሥት በትግራይ ያለውን የሰብዓዊ ሁኔታውን ለማሻሻል በትኩረት እየሠራ መሆኑን አስታወቀ

  • ቪኦኤ ዜና

የኢትዮጵያ መንግሥት በአሁኑ ሰዓት በትግራይ ክልል ያለውን የሰብዓዊ ሁኔታ ለማሻሻል በትኩረት እየሠራ መሆኑን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል ዛሬ እሁድ የካቲት 21/2013 ዓ.ም ባወጣው መግለጫ አስታወቀ። የሰብዓዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ሁሉ ለማዳረስም ሥራውን እያከናወነ የሚገኘውም ከዓለም አቀፍ አጋሮቹ ጋር በመቀናጀት መሆኑን ገልጿል።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ትላንት ቅዳሜ የካቲት 20/2013 ዓ.ም “የጭካኔ አድራጎቶች በኢትዮጵያ ትግራይ ክልል” በሚል ያወጡትን መግለጫ ተከትሎ መግለጫ ያወጣው የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ፤ እስካሁን ለትግራይ ክልልረድኤት ፈላጊዎች የተደረገው 70 በመቶ ድጋፍ በመንግሥት መሸፈኑን እና ቀሪው 30 በመቶ በልማት አጋሮች እና መንግሥታዊ ባለሆኑ ተቋማት ጥረት መሸፈኑ እንዲታወቅ ጠይቋል።

እስካሁን በተሠራው የሰብዓዊ ረድኤት አቅርቦት ሥራም ከ3 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ሰዎች ድጋፍ መደረጉንም አስታውቋል። በተለይ የበለጠ ተጋላጭ በሆነ ሁኔታ ውስጥ ለሚገኙ ሕፃናት እና ሴቶች ቅድሚያ በመስጠት እየተሠራ መሆኑን መሥሪያ ቤቱ ገልጿል። በክልሉየጸጥታው ሁኔታም እየተሻሻለ በመምጣቱ የሰብዓዊ ረድኤት ሠራተኞች ወደ ቦታው ያለገደብ ገብተው ድጋፍ እንዲሠጡ መፈቀዱን በመግለጫው ላይ ጠቅሷል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ አርብ ዕለት ከአሜሪካ ድምፅ ጋር በነበራቸው ቃለ ምልልስ፤ የረኤት ድርጅት ሠራተኞች ከዚህ በፊት በፈቃድ እንዲሄዱ ሲደረግ የነበረው አሠራር ተቀይሮ አሁን “በማሳወቅ” ብቻ እንዲሄዱ እንደተፈቀደላቸውገልፀዋል።

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫም፤ የረድኤት ሠራተኞቹ ሥራቸውን በተቀላጠፈ ሁኔታ እንዲሠሩ የሚያስችል ሁኔታ መፈጠሩን ጠቁሟል።

የዓለም የምግብ ፕሮግራም ዋና ዲሬክተር ዴቪድ ቢዝሊ፤ ቀሪ ሥራዎችን መሥራት እንደሚገባ በመጠቆም የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰብዓዊ ቀውሱ እየሰጠ ያለው ምላሽ እየተሻሻለ መምጣቱን ማረጋገጣቸውን የጠቀሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፤ የዓለም አቀፍማኅበረሰብ አካላም መንግሥት እያደረገ ያለውን ጥረት ከማበረታታ እና ከመደገፍ ይልቅ ሚዛኑን የሳተ መግለጫዎች ማውጣታቸው ተገቢ አይደለም ሲል ወቅሷል።

በሌላ በኩል በትግራይ ክልል ተፈፅሟል የተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችና የተሠራውን የወንጀል ድርጊት በተመለከተ መንግሥት አቋሙን ግልጽ ማድረጉን ያስታወሰው መግለጫው፤ መግሥት የሁሉም ዜጎቹን ደህንነት ለመጠበቅ ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶበኃላፊነት እየሠራ እንደነበር ገልጿል። ጉዳዩን ከሥሩ በመመርመር ወንጀለኞች ለሕግ እንዲቀርቡ ቁርጠኛ የሆነውን አቋሙን ያሳየው ለዚህ እንደሆነም ገልጾ መንግሥት የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች መርማሪ ቡድኖችን ተቀብሎ ከማስተናገድ ባለፈ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ጋርም በትብብር መሥራት የሚቻልበትን ፍንጭ ማሳየቱ በመግለጫው ተዘርዝሯል።

የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ቀደም ሲል ሲያነሳቸው የነበሩ፤ የሰብዓዊ ድጋፍ ያለአንዳች መገደብ ለማድረስ፣ ተፈፅመዋል በተባሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ላይ በገለልተኛ አካል ምርመራ ማድረግ የሚሉ ሁለት ቁልፍ ጉዳዮች ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት አዎንታዊ ምላሽበመስጠት ቁርጠኝነት ማሳየቱን የገለፀው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ፤ የካቲት 20/2013 ዓ.ም የወጣው የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት አንቶኒ ብሊንከን መግለጫ ላይ የተነሳው ሐሳብም በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ ላይ ያጠነጠነ ነው ብለዋል።

ይሁንና የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት፤ በተለይ የአማራ ክልል ልዩ ኃይልን በተመለከተ የሰጠው መግለጫ በአንድ አገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የመግባት ሙከራው እና ተቀባይነት እና አግባብነት የሌለው ነው ብሎታል።

እንዲህ ያሉ ጉዳዮች የኢትዮጵያ መንግሥት ጉዳዮች መሆናቸው እንዲታወቅ ያስገነዘበው መግለጫው፤ እንደ አንድ ሉዓላዊት ሃገር ሕግ ማስከበር በሚያስፈልግባቸው በየትኛውም አካባቢዎች የፀጥታ ኃይል ማሰማራት የኢትዮጵያ መግሥት ኃላፊነት መሆኑ መታወቅአለበት ብሏል። መግለጫው አያይዞም፤ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደማንኛው ሉዓላዊ ሃገር፤ በፌደራል እና በክልል መዋቅሩ ውስጥ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ተጠያቂ የሚሆንባቸው የተለያዩ መዋቅራዊ መርሆዎች እንዳሉት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በአገሪቱ ሕገመንግሥት ላይ የሚጋረጡ ማንኛውንም አደጋዎች የመከላከል እና ሰላምና ደህንነትን የማረጋገጥ ሕገ መንግሥታዊ ግዴታ እንዳለበት በመግለጫው ለዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት ምላሽ የሚሰጠው የውጭ ጉዳይሚኒስቴር መግለጫ፤ የኢትዮጵያን አንድነት ከመከፋፈል አደጋ ለመጠበቅ ሕግ የማስከበር ዘመቻ ላይ የተሰማራው ከዚህ አንፃር ነው ብሏል።

በኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መግለጫ ማጠቃለያም፤ በኢትዮጵያ የወንጀለኛ ቡድኑ ከፍተኛ ክህደት ምክኒያት ተግዳሮቶች መኖራቸውን ገልፆ ሆኖም ኢትዮጵያ ዓለም ዓቀፍ ግዴታዎችን ለማክበር ቁርጠኛ ናት ብሏል። ነገር ግን ዓለም አቀፍ ግዴታን መወጣትእና ኃላፊነትን ማክበር ከሉዓላዊነት መከከበር ጋር ተጣጥመው የሚሄዱ መሆናቸውን መዘንጋት አይገባም ብሏል።