በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለመሆኑ መጪው የዝምባብዌ ፕሬዝዳንት ምናንጋግዋ ማን ናቸው?


መጪው የዝምባብዌ ፕሬዝዳንት ኢመርሰን ምናንጋግዋ በዛሬው ዕለት ከሃራሬው የዛኑ-ፒኤፍ ዋና ጽ/ቤት ደጃፍ ለደጋፊዎቻቸው ሰላምታ ሲሰጡ
መጪው የዝምባብዌ ፕሬዝዳንት ኢመርሰን ምናንጋግዋ በዛሬው ዕለት ከሃራሬው የዛኑ-ፒኤፍ ዋና ጽ/ቤት ደጃፍ ለደጋፊዎቻቸው ሰላምታ ሲሰጡ

የዘጠና ሶስት ዓመቱ የቀድሞው ዝምባብዌ ፕሬዝዳንት ሮበርት ሙጋቤ በመጨረሻው ሥልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቀቁ። በሃያ ዓመታት የሚያንሷቸውና በንጽጽርም ወጣት ተደርገው የተወሰዱት የሰባ አምስት ዓመቱ የቀድሞ ምክትላቸው ኢመርሰን ምናንጋግዋ የፊታችን አርብ ቃለ መሃላ ፈጽመው የሥልጣን መንበሩን ይረከባሉ።

በአፍላ ወጣትነታቸው እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1970ዎቹ በቻይና የሰለጠኑት፥ የዚያን ዘመኑ ሽምቅ ተዋጊ፥ ደም ባፋሰሰውና ለነጻነት በተደረገው ትግል ከሞጋቤ ጋር በመሆን ከተዋጉት ውስጥ አንዱ ናቸው።

ለመሆኑ ዝምባብዌያውያን “አዞው” በሚል ቅጽል መጠሪያ በይበልጥ የሚያውቋቸው አዲሱ ፕሬዝዳንታቸው በእርግጥ ማን ናቸው?

ላለፉት ሰላሳ ሰባት ዓመታት ያችን አገር በጠንካራ መዳፍ ተጭነው የመሯት የፕሬዝዳንት ሮበርት ገብርኤል ሙጋቤ የቀኝ እጅና ብርቱ ተካከላካያቸው ነበሩ። አወዛጋቢው ሁኔታዎች መታየት እስከ ጀመሩበት ቅርብ ጊዜ ድረስ።

በያዝነው ዓመት መጀመሪያ ላይ ፓርቲያቸው ገዢው ዛኑ-ፒኤፍ ማዕከላዊ ዝምባብዌ ላይ ባካሄደው ሰላማዊ የድጋፍ ሰልፍ ተገኝተው ነበር።

“ዛኑ-ፒኤፍ ለሕዝብ የቆመ ግንባሩን የማያጥፍ ፓርቲ ነው። በመሪነቱም ይቀጥላል” ሲሉ ነው፤ በሾና ቋንቋ ምናንጋግዋ ለተሰበሰበው ሕዝብ የተናገሩት።

“እናም ሌሎች ጩሃታቸውን ሊቀጥሉ ይችላሉ። ዛኑ ግን በሥልጣን ይቀጥላል። ከሮበርት ሙጋቤ ጋር ወደፊት። ከዛኑ ፒኤፍ ጋር ወደፊት!” አሉ።

ጥቂት ወራት አለፉ። የተከተለውን ላየ ግን ልዩነቱ ከንጽጽር በላይ ነበር።

ከጥቂት ሳምንታት በፊት ከምክትል ፕሬዝዳንትነት ሥልጣናቸው በሙጋቤ የተነሱትና ባለፈው ሳምንት ጦር ሠራዊቱ ሙጋቤን በቁም እሥር አውሎ ወደ ሥልጣናቸው እንዲመለሱ ያደረጋቸው ምናንጋግዋ፤ ዛሬ ደግሞ የቀድሞ አለቃቸውን (በፈቃዳቸው ከማለት .. በተደረገባቸው ከፍ ያለ ግፊት ተገደው ማለት ይሻላል) ሥልጣን መልቀቅ ተከተሎ የነገዪቱን ዝምባብዌ ሊመሩ ከሽግግሩ ደጃፍ ቆመዋል።

በያዝነው ወር መጀመሪያ ግድም ሙጋቤ በእርሳቸው ላይ “የነበረኝን እምነት አጥቻለሁ” በሚል ከሥልጣን ሲያስወግዷቸው፤ እርምጃው ሙጋቤ እምብዛም ተቀባይነት የሌላቸውን ባለቤታቸውን የሃምሳ ሁለት ዓመቷን ግሬስ ሙጋቤን ወደ ሥልጣን መንበር ለማምጣት አመቺ አጋጣሚ ለመፍጠር ተብሎ የተደረገ ሆኖ ነው፤ የታየው።

ምናንጋግዋ እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር ከ1980ዓም አንስቶ የብሔራዊ የደህንነት ኃላፊነት ጨምሮ በተለያዩ የካቢኔ የሥልጣን ኃላፊነቶች ተሰይመው ከመሥራታቸው በላይ፤ እንደ አውሮፓውያኑ በ2014ዓም ሙጋቤ የቀድሞ ምክትላቸውን ጆይስ ሙጂሩ’ን (የዛሬ ዋና ተቺያቸውን) ከሥልጣን ማንሳታቸውን ተከትሎ ለምክትል ፕሬዝዳንትነት በቁ።

የምናንጋግዋ ለከፍተኛው የሥልጣን እርከን መብቃት ታዲያ በፓርቲው ውስጥ በሁለት ትውልዶች መካከል ለሚታየው ብርቱ የሥልጣን ሽኩቻ ማብቂያ የሚያበጅ ተደርጎም ተወስዷል።

እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር በ1965ዓም “አዞው” የሚለው ቅጽል ሥም በተሰጣቸው በማናንጋግዋ የሚመራው የቀድሞ የነጻነት ዘመን ተዋጊዎች፤ የዛሬዎቹ የፖለቲካ መሪዎች በአንድ ወገን በዚያ ዘመን የተወለዱትና የባለቤታቸውን ሁነኛ የፖለቲካ እንደ ልብ ድጋፍ ያገኙ በነበሩት ግሬስ ሙጋቤ ይመራ የነበረው ደግሞ በሌላው ናቸው።

የኢመርሰን ምናንጋግዋ የአመራር ዘመን ገና ድሮ የጀመረ ይመስላል። የአረጀው የሙጋቤ አመራር መሰናበት የፈጠረው ትኩስ ስሜት ከበረደ በባላ በእርግጥ ለዚያች አገር ሕዝብ አንዳች ዘላቂ ለውጥ ያመጣ ይሆን?

ቆይቶ የሚታይ ነው።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG