በደቡብ አፍሪቃ አስተናጋጅነት እየተካሄደ ያለው የዓለም እግር ኳስ ዋንጫ ውድድር ዛሬ አራተኛ ቀኑን ይዟል። የየምድብ ማጣሪያው ቀጥሏል። ዛሬ በቅድሚያ የተጫወቱት ሆላንድና ዴንማርክ ሲሆኑ፥ ሆላንድ ሁለት ለዜሮ አሸንፎ ከ E ምድብ ሦስት ነጥቦች ይዞ በመሪነት ተቀምጧል።
ጃፓን ደግሞ ባስደናቂ ሁኔታ ጠንካራ ከሚባሉት የአፍሪቃ ቡድኖች አንዱ የሆነውን የካሜሩን ቡድንን አንድ ለዜሮ አሸንፏል።
ጣልያንና ፓራጓይ ከትንሽ ሰአታት በሁዋላ ይጫወታሉ።
ትላንት ስሎቬኒያ እና ጋና በመጀመሪያ ግጥሚያዎቻቸው ድል ተጐናጽፈዋል። ሁለቱም የየምድባቸውን ተጋጣሚዎች 1 ለ 0 ነው ያሸነፉት። የጀርመን ብሄራዊ ቡድን ግን በሰፊ የግብ ልዩነት 4 ለ 0 ነበር ደርባን ስታዲየም አውስትራሊያን የቀጣው።
ጋና የዓለም ዋንጫ ዓርብ ከተጀመረ ወዲህ ከ D ምድቡ የመጀመሪያው የአፍሪካ ባለ ድል ቡድን የሆነው። ደቡብ አፍሪቃ ከሜክሲኰጋር እኩል አንድ ለአንድ ከመለያየቷ በቀር፥ ናይጄሪያና አልጄሪያ በአርጀንቲናና ስሎቪኒያ ተሸንፈዋል።
የ ስሎቬኒያው ሮበርት ኮረን በ 79ኛው ደቂቃ ላይ ከረዥም ርቀት አክርሮ የመታት ኳስ የአልጄሪያውን ግብ ጠባቂ የ ፍውዚ ቻዉቺን እጆች በጥሳ አልፋ ከመረቡ ጋር ተገናኝታለች። በመሆኑም ስሎቬኒያ ከ C ምድቧ በሦስት ነጥብ ትመራለች፥ እኩል አንድ ለአንድ የተለያዩት ዩናይትድ ስቴትስና ኢንግላንድ አንድ አንድ ነጥቦች ይዘው በሁለተኛነት ሲከተሉ፥ አልጄሪያ ወለሉ ላይ የመጨረሻውን ደረጃ ይዛ ትገኛለች።
ለጋና በ 85ኛው ደቂቃ ላይ የተገኘችዋን የፍጹም ቅጣት ምት ወደ ጐል የመነዘራት አሳሞአ ጋያን ይባላል። ብላክ ስታርስ በሴርቢያ ላይ ድል በመጐናጸፋቸው፥ ጋናውያን አክራ ከተማ መንገዶች ላይ ወጥተው ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል።
አሳሞኣ ብቸኛዋን የድል ጐል ከማግባቱም በፊት ሁለት ድንቅ ሙከራዎችን አድርጐ ኳሷ የተመለሰችበት ማዕዘን እየመታች መሆኑ አስቆጭቷል። ቲሙ ባጠቃላይ ያለማቋረጥ ለፈጠረው በርካታ ወርቃማ የግብ ዕድሎች ግን ከደጋፊዎቹ ምርቃት ተችሯል።
ጋና በዚህ አያያዟ ከ D ምድቧ ከጠንካራው የጀርመን ቡድን ጋርወደ ሁለተኛው ዙር የማለፍ ዕድሉ እንዳላት ብዙዎች ያምናሉ። እነዚሁ ብላክ ስታርስ በመጪው ቅዳሜ ደግሞ ከአውስትራሊያ ጋር ረስተንበርግ ስታዲየም በሚያደርጉት ግጥሚያ ተመሳሳይ ድል እንደሚጐናጸፉ ይገመታል።
ከ B ምድብ ጠንካራው የላቲን አሜሪካው የአርጀንቲና ቡድን ናይጄሪያን አንድ ለዜሮ በማሸነፉም ደጋፊዎቹን አስፈንድቋል። ጠንካራ ፉክክር በታየበት ግጥሚያ ጋብሪኤል ሄንዜ ነበር በናይጄሪያው ሱፐር ኢግለስ ቲም ላይ የድሏን ግብ በግንባሩ ገጭቶ ያስቆጠረው። ዋና አሰልጣኙን ዲዬጎ ማራዶናንም ሆነ ደጋፊዎቹን በርግጥም አስፈንድቋቸዋል።
ገና የየምድቡ ማጣሪያው እንኳ ባልተጠናቀቀበትና ግጥሚያዎቹ በቀጠሉበት ባሁኑ ወቅት 32ቱም ቡድኖች ሻምፒዮና የመሆን ዕድል እንዳላቸው መዘንጋት የለበትም። ደጋፊዎቻቸውም የሚፈነድቁት በማጣሪያው አንደኛውን ተጋጣሚያቸውን በማሸነፋቸው ብቻ አይደለም። ለምሳሌ የሴርቢያ ደጋፊዎች ደስታ የተለየ ነው። አገራቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ እንደ አንድ ነፃ አገር ለመሳተፍ በመቻሏ መደሰታቸው አግባብ ነው።
የአለም ዋንጫ ለአንድ ወር ያህል ሲካሄድ ይቀጥላል።