በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በአፍሪካ ቀንድ በተካሄዱ ጦርነቶች ንፁሃን ዜጎች አስከፊ ግፍ ተፈፅሞባቸዋል - ሂዩማን ራይትስ ወች


እ.አ.አ የተገባደደው 2023፣ በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት አፈና እና በጦርነት ውስጥ ከፍተኛ ግፍ የተፈፀመበት ዓመት እንደነበር፣ ዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅት፣ ሂዩማን ራይትስ ወች ሐሙስ እለት ይፋ ያደረገው ሪፖርት አመልክቷል። ቡድኑ በቀጠናው የሚገኙ ተቋማት እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ፣ የሲቪሎችን ደህንነት ለመጠበቅ በቂ ጥረት አለማድረጋቸውን በመግለፅም ተጠያቂ አድርጓል።

እ.አ.አ በ2023 የአፍሪካ ቀንድ መንግስታት መጠነ ሰፊ የሰብአዊ ቀውሶችን እንዳሳለፉ የጠቀሰው ሪፖርት፣ በሱዳን እና በኢትዮጵያ ንፁሃን ዜጎች በጦርነት ስም የተፈፀሙ መጠነ ሰፊ ግፎችን ተቋቁመው ማለፋቸውን እና ምንም አይነት ምርመራ እና ተጠያቂነት አለመኖሩን አመልክቷል።

በሂዩማን ሪይትስ ወች የአፍሪካ ክፍል ምክትል ዳይሬክተር የሆኑት ላቲሺያ ባደር "መንግስታት በጣም መሰረታዊ የሆኑ የጦርነት እና የሰብዓዊ መብት ህጎችን በግልጽ ሲጥሱ አይተናል" ብለዋል።

በሱዳን የጦር ሰራዊት እና በፈጥኖ ደራሹ ቡድን መካከል ሚያዚያ ላይ በተቀሰቀሰው ጦርነት፣ ተፋላሚዎቹ ከባድ የጦር መሳሪያዎችን፣ ህዝብ በሚበዛባቸው አካባቢዎች በተደጋጋሚ መጠቀማቸውን ሪፖርቱ ገልጿል።

ግጭቱን ለመፍታት የተንቀሳቀሱ ተፅእኖ ፈጣሪ መንግስታት እና የቀጠናው ተቋማትም የሰዎችን መብት ማስከበር ላይ የተመሰረተ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ፣ የአጭር ጊዜ መፍትሄ ላይ አተኩረዋል በማለትም ወቅሰዋል።

በኢትዮጵያም፣ በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል በተካሄደው ጦርነት የተሳተፉ አካላት የሰላም ስምምነት ከተፈራረሙ በኃላ፣ በተወሰኑ የትግራይ ክልል አካባቢዎች የሰብዓዊ መብት እና የብዓዊ እርዳታ አቅርቦት መሻሻሉን ባደር ቢያመለክቱም፣ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ተጠያቂነት ለማስፈን በቂ ጥረት አለማድረጉን ሪፖርቱ ገልጿል።

"በተለይ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በአማራ ክልል የመብት ሁኔታ እያሽቆለቆለ መምጣቱን እና ግጭቶች መጨመራቸውን አስተውለናል" ያሉት ባደር "በንፁሃን ዜጎች ላይ እያሳደረ ያለውን ተፅእኖ አያየን ነው። በክልሉ የሚፈፀሙ ህገወጥ ግድያዎችን እና ጾታዊ ጥቃቶችን፣ በተለይ ደግሞ የቀጠለው ግጭት ሰላማዊ ሰዎች መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለማግኘት ባላቸው አቅም ላይ እያደረሰ ያለው አስከፊ ተፅእኖ መዝግበናል" ብለዋል።

እ.አ.አ በ2021 ብቻ ኢትዮጵያ ውስጥ 5.1 ሚሊየን ሰዎች በሀገራቸው ውስጥ የተፈናቀሉ ሲሆን፣ ይህ ቁጥር በአንድ አመት ውስጥ በሀገራቸው ውስጥ በመፈናቀል ከዚህ በፊት ያልተመዘገበ ቁጥር ነው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG