በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አፍሪካ በ3ኛ ዙር ከባድ የሆነ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተንጣለች - የዓለም የጤና ድርጅት


የዓለም የጤና ድርጅት በትናንትናው ዕለት አፍሪካ በሦስተኛ ዙር ከባድ የሆነ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ተንጣለች ሲል አስታወቀ፡፡ ለዚህም በዋናነት በአህጉሪቱ አዳዲስ እና ፈጣን የቫይረሱ ዝርያዎች መስፋፋታቸውን በምክንያትነት አንስቷል፡፡

የዓለም የጤና ድርጅት የቀጠናው ዳይሬክተር ዶ/ር ማታሺዲሶ ሞኤቲ ላለፉት ስድስት ተከታታይ ሳምንታት በአፍሪካ የአዲሱ ቫይረስ ተጠቂዎች ቁጥር በ25 በመቶ ጨምሯል ያሉ ሲሆን አክለውም የሞት ምጣኔውም በ38 ሃገራት 15 በመቶ ጨምሯል ብለዋል፡፡

ዳይሬክተሯ አዳዲሶቹ የቫይረሱ ዝርያዎች በአፍሪካ ስጋቱን ወደ ሌላ ደረጃ አድርሰውታል ይላሉ፡፡ ቫይረሱ ከጨመረባቸው 14 የአፍሪካ ሃገራትም 12 የሚሆኑት በሕንድ የታየው የዴልታ የተሰኘው የኮቪድ-19 ቫይረስ ያሰጋቸዋል ብለዋል፡፡ በአንጻሩ አልፋ እና ቤታ የተሰኙት ዝርያዎች ጥናቱ ከተደረገባቸው 32 ሃገራት በ27 ተገኝቷል፡፡ እስካሁን ድረስም በአፍሪካ ክትባቱን የወሰዱ ሰዎች 1 በመቶ ብቻ ናቸው፡፡ ይሄ አሃዝ በዓለም አቀፍ ደረጃ ክትባቱን ከወሰዱ 11 በመቶ ሰዎች እና በዩናይትድ ስቴትስ እና ብሪታኒያ ከተከተቡ 46 በመቶ የሚሆኑ ሰዎች ጋር በንጽጽር የተወሰደ ነው፡፡

በትናንትናው ዕለት የአፍሪካ ሕብረት የክትባት መልዕክተኛ ስትራይቭ ማቢዩዋ የአውሮፓ እና የዓለም አቀፍ አቅራቢዎች በቃላቸው መሰረት ክትባት ባለማቅረባቸው ተቆጥተዋል፡፡ ማቢዩዋ “የአውሮፓ ሕብረት የክትባት ፋብሪካዎች አሉት የክትባት የማምረቻ ማዕከላቱም በመላው አውሮፓ አሉ፡፡ ነገር ግን አንድ ጠብታ ክትባት እንኳን ወደ አፍሪካ አልላኩም” ሲሉ አውሮፓ ለአፍሪካ ክትባት ለመሸጥ የገባችውን ቃል እንዳላከበረች ገልጸዋል፡፡

የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከል እና መቆጣጠር ማዕከል አፍሪካ ሲዲሲ ዳይሬክተር ጆን ላኬንጋሶንግ የዓለም የጤና ድርጅት በኮቫክስ አማካኝነት 700 ሚሊየን ክትባቶችን ለአፍሪካ ለመላክ ቃል ቢያስገባም እስካሁን ድረስ ወደ አህጉሪቱ የገባው 65 ሚሊየን ክትባት ብቻ ነው ብለዋል፡፡

XS
SM
MD
LG