ወረርሽኙ በስንዴ ምርት ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት ለመቋቋም የእንግሊዝ መንግሥት እና የቢልና ሜሊንዳ ጌትስ ተቋም የአርባ ሚሊየን ዶላር ድጋፍ ሰሞኑን ሰጥተዋል፡፡
(ዲአርአርዳብልዩ) በሚል ምሕፃር የሚጠራውን "የስንዴ ዋግን በዘላቂነት የመቋቋም" ጥረቱን፣ የምርምሩንና የጣልቃ ገብነቱን ሥራ እያስተባበረ ያለው ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሚገኘው ኮርኔል ዩኒቨርሲቲ ነው፡፡ የወረርሽኙን አደገኛነት የሚናገሩት የምርምር ቡድኑ አስተባባሪ ፕሮፌሰር ሮኒ ኮፍማን አሁን የሚገኙት አክራ-ጋና ነው፡፡
በምርምሩ ላይ ለረዥም ዓመታት ቆይተዋል፡፡ የስንዴ ዋግን ችግር ለማስወገድ ብቸኛው መፍትሔ የዘሩን በሽታን የመቋቋም አቅም ማጎልበት መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡ በአውሮፓዊያኑ የዘመን አቆጣጠር በ1970ዎቹ መጀመሪያ የእርሣቸው መምህር የነበሩት ዶክተር ቦርሎግ እንደዚያ ዓይነት ዝርያዎችን ፈጥረው ለመጭዎቹ ሰላሣ ዓመታት ውጤታማ ሆነው የቆዩ ቢሆንም በ1998 ዓ.ም በዩጋንዳ አዲስ በሽታ ተከስቶ እስከ ኢራን መስፋፋቱን ይናገራሉ፡፡
ዩጂ99 የሚባለው ይህ ቫይረስ በነፋስ ተሸካሚነት የሚጓጓዝና በቀን በብዙ ሺህ የሚቀጠሩ ኪሎ ሜትሮችን አቆራርጦ መዛመትና ማሣዎችን መበከል የሚችል መሆኑን ፕሮፌሰር ኮፍማን ጠቁመዋል፡፡
በሽታው በኢትዮጵያ ውስጥም እንደሚታይ የገለፁት ኮፍማን በዚያ እንደሌሎቹ ጎረቤት ሃገሮች ገና ወረርሽኝ አለመሆኑን አመልክተው ያ አስፈሪ ሁኔታ እንዳይደርስ ጠንካራ ርብርብ መደረግ እንዳለበት መክረዋል፡፡ "የስንዴ ዋግ ኢትዮጵያ ውስጥ ወረርሽኝ ከሆነ - አሉ ዶ/ር ኮፍማን - በጣም በርካታ ሰዎች ይጎዳሉ፤ ሰዎች ኑሯቸውንና ጥሪታቸውን ያጣሉ" ብለዋል፡፡ ብዙ ሕይወትም በዚህ ምክንያት ለጥፋት ሊዳረግ እንደሚችሉ ያሣስባሉ፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በኢትዮጵያ ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት የቁሉምሣ ግብርና ምርምር ማዕከል የ"ዲአርአርዳብልዩ" የኢትዮጵያ ድርሻ አስተባባሪ ዶ/ር በዳዳ ግርማም ይህ የስንዳ ዋግ በሽታ ባለፈውም ዓመት ተከስቶ ብዙ ጥፋት ማድረሱን አስታውሰዋል፡፡
ለተጨማሪና ለዝርዝሩ ዘገባውን ያዳምጡ፡፡