በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በወለጋ ዞኖች የጸጥታ ችግር የወባ መድኃኒትን ለማዳረስ ዕንቅፋት መፍጠሩ ተገለጸ


የወባ ትንኝ
የወባ ትንኝ

በኦሮሚያ ክልል፣ በምዕራብ ወለጋ እና በቄለም ወለጋ ዞኖች የቀጠለው የጸጥታ ችግር፣ የወባ በሽታ መድኃኒት ተደራሽነትን በእጅጉ እያስተጓጎለ እንደኾነ የገለጹ ነዋሪዎች እና የጤና ባለሞያዎች፣ “የሰው ሕይውት እያለፈ ነው፤” ሲሉ ለአሜሪካ ድምፅ ተናግረዋል።

የሁለቱ ዞኖች ነዋሪዎች እንደተናገሩት፣ በከተሞች የተከማቹ የወባ መድኃኒቶች እና ሌሎች አቅርቦቶች ቢኖሩም፣ ወደ ገጠር ቀበሌዎች በአግባቡ ለማዳረስና ለአርሶ አደሮች ፈጣን ሕክምና ለመስጠት የጸጥታው ችግር ፈተና እየኾነ ነው።

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ድርጅት ዋና ዲሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ፣ “አማራጭ የትራንስፖርት መፍትሔዎችን በመጠቀም መድኃኒት ለማከፋፈል እየተሠራ ነው፤” ብለዋል።

በምዕራብ ወለጋ ዞን፣ የባቦ ወረዳ ነዋሪ መኾናቸውን የተናገሩት አቶ እድሪስ ሲራጅ፣ ባለቤታቸው፥ “ያለወትሮው ተስፋፍቷል” ባሉት የወባ በሽታ ተይዘው እስከ አሁን የሕክምና አገልግሎት አለማግኘታቸው እንዳሳዘናቸው ገልጸዋል። በአቅራቢያቸው የነበሩ የጤና ኬላዎች በግጭት መውደማቸውን የተናገሩት አቶ እንድሪስ፣ ባለቤታቸውን በግል ለማሳከም ዓቅማቸው ስለማይፈቅድ በቤታቸው እንደተኙ መኾናቸውን ገልጸዋል፡፡

በወለጋ ዞኖች የጸጥታ ችግር የወባ መድኃኒትን ለማዳረስ ዕንቅፋት መፍጠሩ ተገለጸ
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:39 0:00

አቶ እንድሪስ፣ የወባ በሽታ መድኃኒቱ በወረዳ እና በዞን ከተሞች ላይ መኖሩን ቢሰሙም፣ ከርቀቱ የተነሣ ማግኘቱ አዳጋች እንደኾነባቸው አመልክተዋል፡፡ ለወረዳ ከተማው ቀረብ ባሉ አካባቢዎች የፀረ ወባ ኬሚካል ርጭት ቢኖርም፣ መኖሪያ ቤቶችን እያለፉ የሚያደርጉት በመኾኑ፣ በሦስት ቀናት ልዩነት የወባ ትንኞች መታየት ይጀምራሉ፤ ብለዋል፡፡ “አሁን የተጀመረው ርጭት ራቅ ባሉት ቀበሌዎች ውስጥም ቤት ለቤት እየተደረገ፣ የምርመራ እና የመድኃኒት አቅርቦት ቢጀምር፣ ወረርሽኙን በተቻለ መጠን መቀነስ ይቻል ይኾናል፤” ሲሉም ተስፋቸውን ገልጸዋል፡፡

የቄለም ወለጋ ዞን ጊዳሜ ወረዳ ነዋሪ መኾናቸውን የገለጹትና በደኅንነት ስጋት ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ሌላ አስተያየት ሰጭም፣ “በአካባቢው በመንግሥት እና በኦሮሞ ነጻነት ሠራዊት መካከል ግጭት በመኖሩ ወደ ሕክምና ተቋማት መሔድ አስቸጋሪ ነው፤” ይላሉ፡፡

በጊዳሜ ወረዳ ውስጥ የወባ ወረርሽኝ ከሚባለው በላይ አሳሳቢ እንደኾነ ያመለከቱት አስተያየት ሰጪው፣ በየቦታው ይንቀሳቀሳሉ ባሏቸው የሁለቱም ወገን ኀይሎች የተነሣ፣ ሕሙማኑም ኾኑ የሕክምና ባለሞያዎች ወደ ጤና ተቋም ለመሔድ እንደሚሰጉ ገልጸዋል፡፡ “ሕዝቡ በሽታውን እንደያዘ በየቤቱ ተቀምጧል፤ ኹኔታው አሳሳቢ ነው፤” ያሉት ተናጋሪው፣ መንግሥት መድኃኒቱን ለተቸገረው ሕዝብ ለማዳረስ ትኩረት እንዲሰጠው ተማፅነዋል።

የምዕራብ ወለጋ ሰዮ ወረዳ ነዋሪ መኾናቸውን የጠቀሱትና በደኅንነት ስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ ሌላ አርሶ አደርም፣ የመኸር ወቅት ሥራቸውን በወባ ወረርሽኝ ምክንያት መከወን እንዳልቻሉ አመልክተዋል።

በወባ ምክንያት በርካታ አርሶ አደሮች ከእርሻ ሥራ ውጭ መኾናቸውን የተናገሩት አርሶ አደሩ፣ “ቀኑን ሙሉ ተጉዘን የወረዳ ከተማ ብንደርስም፣ በጤና ጣቢያ ላይ መድኃኒት አናገኝም፤ ወደ ግል ጤና ተቋማት ይልኩናል፤ ለዚያ የሚኾን ገንዘብ ግን ስለሌለን መድኃኒት መግዛት አንችልም፤” ብለዋል፡፡ መንግሥት መድኃኒት እያሰራጨ ስለመኾኑ መግለጹን የጠቀሱት አርሶ አደሩ፣ ለተጎዳው የኅብረተሰብ ክፍል መድረሱን እንዲያረጋግጥ ጠይቀዋል፡፡

የኢትዮጵያ መድኃኒት አቅራቢ ድርጅት ዋና ዲሬክተር ዶክተር አብዱልቃድር ገልገሎ በበኩላቸው፣ የጸጥታ ችግር ባለባቸው አካባቢዎች ላይ አማራጭ መንገዶችን በመጠቀም መድኃኒት እያሰራጩ መኾናቸውን አስታውቀዋል።

ዶክተር አብዱልቃድር፣ ከሦስት ወራት ወዲህ፣ ከመደበኛ ስርጭት በተጨማሪ የወባ መድኃኒት እየተሰራጨ መኾኑንም አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር መረጃ፣ በ2016 ዓ.ም. ከ5ሚሊዮን 200ሺሕ በላይ ሰዎች በወባ በሽታ መያዛቸውን ያመላክታል።

የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዩኤን-ኦቻ፣ በቅርቡ ባወጣው ሪፖርቱም፣ በኢትዮጵያ እ.አ.አ ከጥር ወር እስከ ሰኔ ወር ባሉት ስድስት ወራት ውስጥ ብቻ፣ ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች በወባ መያዛቸውን አስፍሯል። ከሕሙማኑም 35 በመቶዎቹ፣ በኦሮሚያ ክልል እንደሚገኙ ኦቻ በዘገባው ጠቁሟል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG