የዩናይትድ ስቴትስ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ጠበቆች ቡድን፣ የፌዴራል ዐቃቤ ሕግ፣ የቅርብ ጊዜውን ክሥ አስመልክቶ፣ በይፋ በሚያጋሩት መረጃ ላይ ገደብ እንዲጣል ያቀረቡትን ጥያቄ እንደሚቃወሙ ተናግረዋል፡፡ ጉዳዩ፣ የበለጠ ቆንጣጭ እየኾነ የመጣ ይመስላል፡፡ ቀስ በቀስም፣ ዓለም አቀፍ አስተያየት እየተደመጠ ነው፡፡
ለፕሬዚዳንታዊ ሥራቸው እንደገና የሚወዳደሩት ትረምፕ፣ ባለፈው ቅዳሜ፣ በደቡብ ካሮላይና ኮሎምቢያ ውስጥ ባደረጉት የምርጫ ቅስቅሳ፣ በቅርቡ የተመሠረተባቸውን ክሥ፣ ይህ “ማጭበርበር ነው፤” ሲሉ ገልጸውታል፡፡
ባለፈው ሳምንት፣ እ.አ.አ. በ2020 የደረሰባቸውን የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሽንፈት ለመቀልበስ አሢረዋል፤ የሚል ክሥ የተመሠረተባቸው ትረምፕ፣ ፍርድ ቤት ቀርበው ነበር፡፡
በኤቢሲ ቴሌቭዥን፣ “በዚኽ ሳምንት” በሚለው ፕሮግራም ላይ የቀረቡት የትረምፕ ጠበቃ ጆን ላውሮ፣ ዐቃቤ ሕግ ይህን ለማረጋገጥ ከፍተኛ ችግር ይገጥመዋል፤ ብለዋል፡፡
ጠበቃው አክለውም፣ “በማጭበርበር ወይም ኾነ ብለው በወንጀል ጥፋተኝነት ስሜት ያድርጉት አያድርጉት፣ ያን ማረጋገጥ ጨርሶ አይቻላቸውም፤” በማለት ተናግረዋል፡፡
ትረምፕ፣ እርሳቸውን የሚተናኮል ማናቸውንም ሰው እንደሚበቀሉ የዛቱበት የሚመስል ዐይነት መረጃ፣ ኢንተርኔት ላይ ካወጡ ወዲህ፣ ዐቃቤ ሕጎች፥ ትረምፕ እና ጠበቆቻቸው፣ ክሡን አስመልክቶ ለሕዝቡ በይፋ በሚያጋሩት መረጃ ላይ ገደብ እንዲያኖሩ፣ የፌዴራል ዳኛውን ጠይቀዋል፡፡
የትረምፕ ጠበቆች ቡድን፣ ስለ ጉዳዩ ምላሽ ለመስጠት፣ እስከ ዛሬ ሰኞ ድረስ ጊዜ አላቸው፡፡
የሕግ ጠበቃው ጆን ላውሮ፣ ሲኤንኤን ላይ ቀርበው በሰጡት አስተያየት፣ “ፕሬሱ እና የአሜሪካ ሕዝብ፣ በምርጫው ወቅት፣ በክሡ ላይ ያለው መረጃ ምን እንደኾነ የማወቅ መብት አላቸው፡፡ ማስረጃው በሌላ መንገድ የተጠበቀ እስካልኾነ ድረስ፣ ያን እንቃወማለን፤” ብለዋል፡፡ለፕሬዚዳንታዊ ሥልጣን የሚወዳደሩት የቀድሞ ምክትል ፕሬዚዳንት ማይክ ፔንስ፣ በጉዳዩ ላይ ምስክርነታቸውን እንዲሰጡ ሊጠሩ ይችላሉ፡፡
እኤአ በ2020፣ የምርጫውን ውጤት እንዲቀለብሱ፣ በትረምፕ ጠበቆች እንደተጠየቁ የገለጹት ፔንስ፣ ለምን አሉታዊ እንደኾነ፣ ሲኤንኤን ላይ ቀርበው አስረድተዋል፡፡
“ማንም፣ ምክትል ፕሬዚዳንት ወይም ሌላ ማናኛውም ሰው፣ የአሜሪካን ፕሬዚዳንት የመምረጥ መብት ሊኖረው አይገባም፡፡ ፕሬዚዳንቱ፣ የአሜሪካ ሕዝብ እና የአሜሪካ ሕዝብ ብቻ ነው፤” ብለዋል ፔንስ፡፡
ትላንት እሑድ ጧት፣ በተላለፉ በርካታ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞች ላይ የቀረቡት የትረምፕ ጠበቃ ጆን ላውሮ፣ የቀድሞ ፕሬዚዳንት ፔንስ፣ የ2020ውን ምርጫ ውጤት እንዲቀለብሱ[ትረምፕ] አልጠየቋቸውም፤ ብለዋል፡፡
ፕሬዚዳንቱ የፈለጉት ነገር ቢኖር፣ “ተጭበርብሯል” ያሉትን ምርጫ፣ ክፍለ ግዛቶች እስኪያጣሩ ድረስ፣ ምክትል ፕሬዚዳንቱ የድምፅ ማረጋገጫውን የምስክር ወረቀት(ሰርቲፊኬት) “እንዲያዘገዩት” ብቻ ነው በማለት ተናግረዋል፡፡
ላውሮ አያይዘውም፣ “ፔንስ እ.ኤ.አ. ጥር 6 ቀን 2021 የነበረውን የማረጋገጫ ሰርተፊኬት እንዲያዘገዩት፣ በትረምፕ መጠየቃቸው፣ ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ነው፤” ብለዋል፡፡
ትረምፕ የገጠማቸውን የሕግ ችግሮች አስመልክቶ፣ ዓለም አቀፍ አስተያየቶች እየተደመጡ ነው፡፡ ይህ መኾኑ፣ በዋሽንግተን ዩኒቨርስቲ የፖለቲካ ሳይንስ መምህር ፕሮፌሰር ጀምስ ሎንግን አላስደነቃቸውም፡፡
“በተወሰኑ አገሮች ያሉ አንዳንድ መሪዎች፣ ከትረምፕ ሰብእና የመነጩ አንዳንድ ስሕተቶችን፣ እስከ አሁን ተቀብለው ወደ ራሳቸው የአገር ውስጥ ጉዳይ ጨምረዋል፤” ያሉት ሎንግ፣ “አሁን እንደማስበው፣ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋራ ያላቸው ጤናማ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲቀጥል ጥረት በሚያደርጉበት ወቅት፣ አሁን የዚኽን ነገር መጨረሻ በአርምሞ ቢመለከቱ ብልህነት ነው፤” ሲሉ መክረዋል፡፡
ምንም እንኳን፣ በውጭ አገር ያሉ ሰዎች፣ ስለ ትራምፕ ጉዳይ መስማት የሰለቻቸው ወይም ስለ እርሱ መስማቱ እና ማሰቡ ለእነርሱ ምንም የሚያስከተለው ነገር ባይኖርም፣ የትረምፕ የቅርብ ጊዜ ክሥ በከባዱ መታየት አለበት፤ ሲሉ፣ በሃርቫርድ የኬኔዲ የትምህርት ማዕክል፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነት የተካኑት ካትሪን ሲኪንክ ይናገራሉ፡፡
“ዴሞክራሲ ከሌለ ወይም ዴሞክራሲው ድክመት ካለበት የሰብአዊ መብት ይዳከማል፡፡ ስለዚኽ ይህ ጉዳይ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በአግባቡ ከተያዘ፣ ሌሎች አገሮችም በጊዜ ሒደት ውስጥ ትኩረት ይሰጡታል፤ ብዬ አምናለኹ፤” ብለዋል፡፡
በእርሳቸው አስተያየት፣ ጉዳዩ፥ ዩናይትድ ስቴትስ ሕግን ተጠቅማ ችግሮቿን እንዴት እንደምታስወግድ የሚታይበት ምሳሌ ይኾናል፡፡
የቪኦኤዋ ቬሮኒካ ባልደራስ የፖለቲካ ተንታኞችን በማነጋገር ያጠናቀረችውን ዘገባ ነው።
መድረክ / ፎረም