ዓለም አቀፉ የፀረ ትንባሆ ቀን፣ በየዓመቱ ግንቦት 23 ይታሰባል። በዛሬው ዕለትም፣ “ትንባሆ ሳይኾን ምግብ አልሙ” በሚል መሪ ቃል ታስቧል። እ.ኤ.አ በ2020 የተደረገ አንድ ጥናት፣ በዓለም ላይ ከ20 በመቶ በላይ ሕዝብ፣ አጫሽ እንደኾነ አስታውቋል፡፡
በዩናይትድ ስቴትስ ቴክሳስ ግዛት ፎርወርዝ ነዋሪ የኾኑት፣ የደረት እና የመተንፈሻ አካላት ስፔሻሊስት፣ መምህር እና የፀረ ትንባሆ አንቂው ዶር. ደረጀ ሣህሌ አዮ፣ ከአሜሪካ ድምፅ ጋራ ቆይታ አድርገዋል፡፡
ዶር. ደረጀ፣ አጫሽነት፥ ለካንሰር፣ ለልብ እና በሴቶችም ላይ መካንነትን ያስከትላል፤ ይላሉ፡፡ በተለይም፣ የማያጨሱ ነገር ግን ለትንባሆ ጢሶች የተጋለጡ ሁለተኛ ደረጃ አጫሾች እንዲጠነቀቁ ያሳስባሉ፡፡
አንድ ሺሻ፣ ከ10 ትንባሆ እኩል እንደኾነ የገለጹት ባለሞያው፣ ባያጨሱም ከሚያጨሱት ጋራ አብረው የሚኾኑቱ፣ እኩል በኩል ተጎጂዎች እንደኾኑ አስረድተዋል፡፡ ዶር. ደረጀ፣ በአፍሪካ፣ ሲጃራ እና ሺሻ፣ በወጣቶች ላይ በይበልጥም በዩናይትድ ስቴትስ በሚኖሩ፣ የኢትዮ ኤርትራውያን ወጣቶች ላይ እያሳደሩት ባለው ጫና፣ እንዲሁም ከሱሶቹ መላቀቅ በሚቻልበት ኹኔታ ላይ ምክራቸውን ይሰጣሉ፡፡