“በደርዘን ይቆጠራሉ፣ በሞተር ብስክሌት ነው የመጡት፡፡ ወዳገኙት አቅጣጫ ይተኩሱ ነበር። የትምህርት ቤቱን መውጪያ መግቢያ ዘግተው ከበቡ። ከከተማው የሚያስገባውንም ሆነ ሌሎችንም መንገዶች ሁሉ ዘጉ። ከሁለት መቶ በላይ የአንደኛ ደረጀ ተማሪዎችን ከኩሪጋ ቁጥር አንድ ት/ቤት ይዘው ሄዱ” ሲሉ ኑራ አህመድ የተባሉ ረዳት መምህር በዕለቱ የነበረውን ሁኔታ ገልጿል።
ቅዳሜ ከታገቱት ውስጥ ቢያንስ አንድ መቶ የሚሆኑቱ ከ 12 ዓመት በታች ዕድሜ ያላቸው ሲሆን፣ የትምህርት ቀናቸውን ሊጀምሩ በሚዘጋጁበት ወቅት ተከበው ወደ ጫካ መወሰዳቸውን የኩሪጋ ከተማ ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ልጆቹን ለማዳን የሞከረ አንድ ግለሰብ መገደሉንም የትምህርት ቤቱ አስተዳዳሪዎች አስታውቀዋል። ራሺዳት ሃምዛ የተባሉ እናት ከስድስት ሎጆቻቸው አምስቱ ታግተው ተወስደዋል። ከ7 እስከ 18 ዓመት ዕድሜ ያላቸው ልጆቻቸው በሰላም እንዲመለሱላቸው አጥብቀው ይማፀናሉ።
“ምን እንደምናደርግ አናውቅም፣ ግን በፈጣሪ እናምናለን። ጥበቃ የለንም፣ ት/ቤቱን የሚጠብቁ ወታደሮችም ሆኑ ፖሊሶች የሉም” ሲሉ ተናግረዋል።
ለተማሪዎቹ መጠለፍ እስከ አሁን ኃላፊነቱን የወሰደ ቡድን የለም። የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ጠለፋውን የፈፀሙት፣ ቤዛ ክፍያ ለማግኘት ተመሳሳይ እገታ የሚፈጽሙትና በናይጄሪያ ሰሜን ምዕራብ እና ማዕከላዊ የአገሪቱ ክፍል የሚገኙ የታጠቁ ወሮበሎች ናቸው።
በናይጄሪያ ሰሜናዊ ክፍል ሴቶች፣ ሕፃናት እና ተማሪዎች ለቤዛ ክፍያ ሲባል የሚታገቱ ሲሆን፣ የሚለቀቁትም ክፍያውን ከፈፀሙ በኋላ ነው።