በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ቪኦኤ አማርኛ - የቅዳሜ፤ ግንቦት 22/2012 ዜና


በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ተጋላጭ ከአንድ ሺህ በላይ ሆነ

ኢትዮጵያ ውስጥ ለኮሮናቫይረስ መጋለጣቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር ከአንድ ሺህ ስድሣ መብለጡን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል።

የኮቪድ 19 ሞት ቁጥር ስምንት መድረሱን በጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ፊርማ የወጣው የዛሬ መግለጫ ያሳያል።

መግለጫው ዛሬ እስከወጣበት ጊዜ በነበሩት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረጉ 5 ሺህ 34 የላብራቶሪ ምርመራዎች ለቫይረሱ መጋለጣቸው የተረጋገጠው ዘጠና አምስት ሲሆን ኢትዮጵያ ውስጥ የኮሮናቫይረስ ተጋላጮች አጠቃላይ ቁጥር ዛሬ 1063 ደርሷል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኮቪድ 19 የዓለም መዛመት ቁጥር ወደ ስድስት ሚሊየን መጠጋቱን ዓለምአቀፉን ሁኔታ በቅርብ እየመዘገበ ያለው የጆንስ ሃፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የኮሮናቫይረስ መረጃ ማዕከል ዛሬ አስታውቋል።

በማዕከሉ መረጃ መሠረት በዓለም ዙሪያ 365 ሺህ 800 ሰው በኮቪድ 19 ምክንያት ሞቷል።

ሠንጠረዡን እየመራች ባለችው ዩናይትድ ስቴትስ የተጋላጩ ቁጥር አንድ ሚሊየን 750 ሺህ፤ የሞቱ ቁጥርም አንድ መቶ ሁለት ሺህ 900 መድረሱን ዩኒቨርሲቲው አመልክቷል።

ከ135 ሺህ በላይ ተጋላጮች እንዳሉባት ዛሬ ጠዋት በተነገረው አፍሪካ ከሦስት ሺህ ዘጠኝ መቶ በላይ ሰው በኮቪድ 19 ምክንያት መሞቱ ተገልጿል።

ከቤይሩት ተጨማሪ 323 ሃገራቸው ገቡ

ኢትዮጵያዊያን ተመላሾች ቤይሩት ሃሪሪ ዓለም አቀፍ አይሮፕላን ጣቢያ ላይ
ኢትዮጵያዊያን ተመላሾች ቤይሩት ሃሪሪ ዓለም አቀፍ አይሮፕላን ጣቢያ ላይ


ቤይሩት ውስጥ ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ተመዝግበው ሲጠባበቁ የነበሩ ተጨማሪ 323 ኢትዮጵያዊያን ዛሬ ተመልሰዋል።

ኢትዮጵያዊያኑ የተመለሱት ለመጓጓዣና ለተለያዩ ወጭዎች የከፈሉት 550 ዶላር ተመልሶላቸው መሆኑን በሊባኖስ የኢትዮጵያ በሊባኖስ የኢትዮጵያ ቆንስላ ጄነራል አስታውቋል።

ከሁለት ቀናት በፊት እንዲመለሱ የተደረገውን ጨምሮ አጠቃላይ ቁጥር 658 መድረሱን የቆንስላ ጄነራል ፅህፈት ቤቱ በፌስ ቡክ ገፁ ላይ ባወጣው ዝርዝር መግለጫ ላይ አመልክቷል።

ኢትዮጵያዊያኑ ከቤይሩት ከመነሳታቸው በፊት አስፈላጊው የኮቪድ 19 ፍተሻ እንደተደረገላቸውና አዲስ አበባ ሲደርሱም ለይቶ ማቆያ ውስጥ የሚቆዩባቸው ሁኔታዎች የተመቻቹላቸው መሆኑን፤ የአሥራ አራት ቀናት የቆይታ ጊዜያቸውን ከጨረሱ በኋላም እስከመኖሪያ ቀዬዎቻቸው የሚደርሱበትና ከየማኅበረሰባቸው ጋር የሚቀላቀሉባቸው ዝግጅቶች መደረጋቸውንም ፅህፈት ቤቱ ገልጿል።

የጆርጅ ፍሎይድ መገደል ዓለም አቀፍ ንግግር እየሆነ ነው

በዩናይትድ ስቴትስ ማዕከላዊ ምዕራብ ግዛቷ ሚኔሶታ ከተማ ሜኔአፖሊስ ውስጥ በነጭ ፖሊሶች የተገደለው ጥቁር አሜሪካዊ ጆርጅ ፍሎይድ ጊዳይ ባስነሳው ቁጣ ተቃዋሚዎቹ በከተማዪቱ በተለያዩ አካባቢዎች በሚገኙ ተቋማት ላይ እሳት አንስተዋል።

በሌላ በኩል ግን ቀድሞ ባልታየ ሁኔታ አፍሪካ ዋና ከተሞች ውስጥ የሚገኙ የዩናይትድ ስቴትስ ኤምባሲዎች የበረታ ይዘት ያላቸውን መግለጫዎች እያወጡ ናቸው። አሜሪካ ምድር ላይ የተፈፀመው አድራጎት በመላ አፍሪካ ቀጣና ቅሬታን ማጫሩም ተዘግቧል።

የኤምባሲዎቹ መግለጫዎች እየወጡ ያሉት የአፍሪካ ኅብረት ሊቀመንበር መሳ ፋኪ ማሃማት በጆርጅ ፍሎይድ ላይ የተፈፀመውን አድራጎት በዩናይትድ ስቴትስ ጥቁር ዜጎች ላይ እየቀጠለ ያለ የመድልዎ አድራጎት ሲሉ ውግዘት ካሰሙ በኋላ ነው።

በኮንጎ የአሜሪካ አምባሳደር ማይክ ሃመር ባወጡት መልዕክት የጆርጅ ፍሎይድ ሜኔአፖሊስ ውስጥ በአሳዛኝ ሁኔታ መገደል የረበሻቸው መሆኑን ጠቁመው የሃገራቸው የፍትሕ ሚኒስቴር ለጉዳዩ ከፍተኛ ቅድሚያ ሰጥቶ ወንጀል ምርመራ እያካሄደበት መሆኑን ገልፀዋል።

ኬንያ፣ ዩጋንዳና ታንዛኒያ ያሉት የአሜሪካ ኤምባሲዎችም የየራሳቸውን መልዕክቶች አውጥተዋል።

እንድ ነጭ ፖሊስ አንገቱ ላይ በጉልበቱ ተጭኖት በደረሰበት ጉዳት ምክንያት ጥቁሩ ጆርጅ ፍሎይድ መሞት በመላ ዩናይትድ ስቴትስ ተቃውሞዎችን እያቀጣጠለ መሆኑ ተዘግቧል።

ሰልፈኞቹ ሚኔአፖሊስ ውስጥ የንግድ ተቋማትን፣ ተሽከርካሪዎችንና ፖሊስ ጣቢያ በእሳት አጋይተዋል።

በሜኔአፖሊስና በአጎራባቿ ሴንት ፖል ከተሞች 500 ብሄራዊ ዘብ የተሠማራ ሲሆን ነገ ቁጥሩ ወደ 1700 ከፍ እንደሚል ተገልጿል።

የቅዳሜ፤ ግንቦት 22/2012 ዓ.ም. የቪኦኤ አማርኛ ዜና
please wait

No media source currently available

0:00 0:06:46 0:00


XS
SM
MD
LG