አሁን በአገሪቱ ያለው ሕግ፣ ውርጃን የሚፈቅደው የወላጇ ጤናም ሆነ ሕይወት አደጋ ላይ የወደቀ ሆኖ ሲገኝ ብቻ ነው። ይህም ሴቶች ሌሎች አደገኛ አማራጮችን እንዲጠቀሙ አስገድዷል። ሃሪም ሻይቡ ከእነዚህ አንዷ ናቸው። “የተለያዩ እጽዋቶች እና ሳሙና ማህጸኔ ውስጥ ተጨመረ። ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ደም ይፈሰኝ ጀመር። በዚህ መልክ ነው እርግዝናው የተቋረጠው” ብለዋል ሃሪም።
የማላዊ የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እንደሚለው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2022 እና 2023 ዓ.ም የተሰበሰቡ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት፣ በተጠቀሱት ሁለት ዓመታት 35 ሺሕ አደገኛ የጽንስ ማቋረጦች ተፈጽመዋል። ከአደገኛው ሙከራ በኋላ ጤናቸው ስለሚታወክ፣ ሴቶቹ ወደ መንግስት ሆስፒታል በመምጣት ሕክምና ለማግኘት ይገደዳሉ።
“ሰዎች በራሳቸው ላይ ውርጃ እንደሚፈጽሙ ሪፖርቶች ሰምተናል። ይህም ወደ ተለያዩ ውስብስብ የጤና ችግሮች ያመራል። የደም ማነስ ከመፍጠሩ በተጨማሪ፣ ማሕጸንን ሊቀድ እና ውስብስብ ችግር ሊፈጥር ይችላል። በአጠቃላይ አባለ ወሊድ አባል አካላትን ሊጎዳ ይችላል” ብለዋል ቺሜምዌ ሳምባሊካ የተባሉ የካሙዝ ሆስፒታል ነርስ። የሴቶች መብት አቀንቃኞች፣ የጽንስ ማቋረጥ ሕግ እንዲሻሻልና ሴቶች አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኙት ጽንስ የማቋረጥ መብት እንዲኖራቸው ግፊት በማድረግ ላይ ናቸው። በተጨማሪም፣ የሕግ ረቂቁ፣ በሴቷ የእምሮም ሆነ የአካል ጉዳት የሚያስከትል ከሆነ ወይም በአስገድዶ መደፈር እንዲሁም በዘመድ መሃል የሚፈጸም ጽንስ ከሆነ እንዲቋረጥ ይፈቅዳል።
“የሚያሳስበን ሴቶች ሕይወታቸውን እያጡ መሆኑ ነው። ሆስፒታሎቻችን ሊያድኗቸው ሲችሉ፣ ሴቶቻችን እየሞቱ ነው። አንድ ነገር ማድረግ ስንችል ሲቶቻችን ሲሞቱ ዝም ብለን ማየት አለብን?” ይላሉ ዶ/ር ማቲዎስ ግዋሌ የፓርላማው የጤና ኮሚቴ ሊቀመንበር። ረቂቅ ሕጉ ከስምንት ዓመታት በፊት ይፋ ሲሆን፣ የሃይማኖት ቡድኖች ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ አጥብቀው ተቃውመውት ነበር።
የረቂቅ ሕጉ ደጋፊዎች ደግሞ ፓርላማው በረቂቁ ላይ ክርክር እንዲያደርግ ከመግፋት ባሻገር፣ በገጠርማ አካባቢዎች ቤት ለቤት በመዘዋወር፣ ከሕክምና ማዕከላት ውጪ የሚፈጽም ውርጃን አደገኛነት በማስተማር ላይ ይገኛሉ።