በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በቶሮንቶ የኤርትራውያን ፌስቲቫል ላይ በተፈጠረ ግጭት ሰዎች ተጎዱ


ፎቶ ፋይል፦ ኤርትራ የባህል ፌስቲቫል ሰሜናዊ ስቶክሆልም
ፎቶ ፋይል፦ ኤርትራ የባህል ፌስቲቫል ሰሜናዊ ስቶክሆልም

ባለፈው ሳምንት መገባደጂያ በካናዳዋ ቶሮንቶ ከተማ በመካሄድ ላይ በነበረው የኤርትራ የባህል ፌስቲቫል፣ በተሳታፊዎች እና በመንግስቱ ተቃዋሚዎች መካከል በተነሳ ግጭት አደጋ የደረሰባቸው ዘጠኝ ሰዎች ወደ ሆስፒታል ተወስደው በህክምና ሲረዱ፣ የሥነ ስርዓቱ አዘጋጆችም በከተማው አስተዳደር የተሰጣቸውን ፍቃድ እንዲነጥቁ ምክንያት ሆኗል።

የከተማይቱ ከንቲባ ኦሊቪያ ቻው ብጥብጡን “ተቀባይነት የሌለው” ሲሉ ጠርተውታል።

ከተጎዱት ሰዎች ስምንቱ፣ የደረሰባቸው አደጋ ለህይወት የማያሰጋ መሆኑን ያመለከተው የከተማይቱ ፖሊስ፣ በትዊተር ገፁ ባሰፈረው መልዕክት፣ በስለት የተወጉ አንድ ግለሰብ ግን የደረሰባቸው ጉዳት ከባድ መሆኑን አመልክቷል። የተቀሩት ስምንቱ በምን እንደተጎዱ ፖሊስ የገለጸው ነገር የለም።

ፖሊስ በተጨማሪም በከተማይቱ ምዕራብ ዳርቻ ወደሚገኘው እና ፌስቲቫሉ ገና እንደጀመረ ወደ ትርምስ ወዳመራው ኧርልስኮርት ፓርክ ወደተባለው ሥፍራ የአድማ በታኝ ኃይል ለማሰማራት መገደዱ ተዘግቧል። ከጠዋቱ አራት ሰዓት ግድም ላይ በመጠነኛ ግብግብ

የጀመረው ያለመግባባት፣ ቀኑን ሙሉ ውጥረት ሰፍኖበት መዋሉም ተመልክቷል።

ብጥብጡ በመቀጠሉም ከምሽቱ አራት ሰዓት ላይ ለሰዎች ደህንነት ሲባል ፌስቲቫሉ እንዲይቀጥል መደረጉን የቶሮንቶ ከተማ የሚዲያ ግንኙነት ክፍል ሥራ አስኪያጅ ራስል ቤከር ይፋ ባደረጉት መግለጫ አስረድተዋል። የተባለው ፍቃድ መጀመሪያ የተሰጠው ከቅዳሜ እስከ ሰኞ ላለው ጊዜ እንዲያገልግል እንደነበርም ቤከር አክለው አመልክተዋል።

በዩናይትድ ስቴትሷ የሲያትል ከተማም በተመሳሳይ የተቀሰቅሰ ብጥብጥ ለትርኢቱ የተዘጋጁ ድንኳኖች ቢፈርሱም፤ ድርጊቱ የተፈጸመው ሥነ ስርዓቱ ከመጀመሩ አቀድሞ ስለነበር፣ በዓሉ በታቀደለት መርሃ ግብር መሰረት ከፍተኛ ጥበቃ ተደርጎለት ቀጥሏል።

በሌላ ተያያዥ ዜና ባለፈው ሳምንት በስዊድኗ ዋና ከተማ ስቶክሆልም በተካሄደ ሌላ የኤርትራ ፌስቲቫል ላይ ተመሳሳይ ውጥረት የሰፈነበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበር ተዘግቧል። ቁጥራቸው አንድ ሺህ የተገመቱ ተቃዋሚዎች ዝግጅቱን ለማስተጓጎል ባደረጉት እንቅስቃሴም በርከት ያሉ ሰዎች መቁሰላቸው ታውቋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG