በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የጆ ባይደን እና የፖል ራያን “እሰጣገባ”


የአሁኑ የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት (ዴሞክራት) ጆ ባይደን እና የዊስከንሰኑ እንደራሴ የሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጩ ምክትል ፕሬዚዳንት ፖል ራያን
የአሁኑ የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት (ዴሞክራት) ጆ ባይደን እና የዊስከንሰኑ እንደራሴ የሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጩ ምክትል ፕሬዚዳንት ፖል ራያን

የፊታችን ጥቅምት 27 ቀን 2005 ዓ.ም ለሚካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ አጠቃላይ ምርጫ የሚደረገው ፕሬዚንዳታዊ ፉክክርና ዘመቻ አካል የሆነው የዕጩዎቹ ምክትል ፕሬዚዳንቶች የፊት ለፊት ክርክር ሐሙስ፤ ጥቅምት 1 ምሽት ላይ ተካሂዷል፡፡


please wait

No media source currently available

0:00 0:04:39 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ


please wait

No media source currently available

0:00 1:34:33 0:00
ቀጥተኛ መገናኛየአሁኑ የዩናይትድ ስቴትስ ምክትል ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን በሠነዘሩት ጠንከር ያለ ቃል፤ የኦባማ አስተዳዳር የሃገሪቱን ምጣኔ ኃብት መጠገኑን እንዲቀጥልበት የሪፐብሊካን ፓርቲውን ፕሬዚዳንታዊ ዕጩ ምክትል ፖል ራያንን ጨምሮ በተወካዮች ምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያላቸው ሪፐብሊካን እንደራሴዎች ከጎዳናው ዘወር እንዲሉ ጠይቀዋቸዋል፡፡

በማዕከላዊ ደቡብ ዩናይትድ ስቴትሷ ኬንተኪ ግዛት በአንድ አነስተኛ ኮሌጅ ውስጥ በተካሄደውና በቴሌቪዥን በመላ ሃገሪቱ በተሠራጨው ክርክር አሜሪካ ለገባችበት የኢኮኖሚ ድቀት ሪፐብሊካኑን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡


“ከሰማይ ዱብ ያለ ይመስልና ‘የአንድዬ ያለህ! ከየት የመጣ ነው?!’ እንደሚሉ ሁሉ ስለዚህ እጅግ የከበደ የምጣኔ ኃብት ድቀት ይናገራሉ፡፡ ሁለት ጦርነቶችን በብድር ለመዋጋት ከወሰነው ሰውዬ የመጣ ነው፡፡” ሲሉ ባይደን ወርፈዋል፡፡

ራያንም በበኩላቸው በሰጡት የአፀፋ ምላሽ ፕሬዚዳንት ኦባማና የምክር ቤቱ አባላት የሆኑ ዴሞክራቶች በ2008 ዓ.ም ወደ ሥልጣን በዘለቁ ጊዜ ያኔ ያሻቸውን ሊያደርጉ የሚያስችላቸው የአንድ ፓርቲ የበላይነት እንደነበራቸው አስታውሰዋቸዋል፡፡ “ያኔ የኢኮኖሚ ማነቃቂያው ካለፈ ምጣኔ ኃብቱ በአራት ከመቶ እንደሚያድግ አስተዳደሩ ለአሜሪካዊያን ቃል ገብቶ ነበር፤ እያደገ ያለው ግን በ1.3 ከመቶ ብቻ ነው” ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በውጭ ጉዳይ ፖሊሲ ላይ በተደረገው ክርክርም ባለፈው ወር ሊብያ በነበሩት የአሜሪካ አምባሣደር ላይ የደረሰውን አደጋ “እጅግ አሣዛኝ አጋጣሚ ነው” ብለውታል ባይደን፡፡ ማንኛውም በወቅቱ የተሠራ ሥህተትም አይደገምም ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡

የኦባማ አስተዳደር ቤንጋዚ ውስጥ በቂ የደህንነት ጥበቃ አላደረገም ሲሉ ሪፐብሊካኑ ዕጩ ምክትል ፕሬዚዳንት በብርቱ የነቀፉ ሲሆን በወቅቱ የተፈፀመው የሽብር ጥቃት መሆኑን ለማመን እንኳ አስተዳደሩ ሁለት ሣምንት እንደፈጀበት ተናግረዋል፡፡“ፓሪስ ያሉት አምባሣደራችን የባሕር ወለድ ኮማንዶ ንዑስ ኃይል አጀብ አላቸው፤ የታጠቀ የአልቃይዳ ጋንታ እንዳለባት በምናውቃት ሊብያ ያሉ አምባሣደራችን ተመሣሣይ የባሕር ወለድ ኮማንዶ ንዑስ ኃይል ጋሻ ጃግሬ ሊደረግላቸው አይገባም ነበርን?” ብለዋል፡፡

ቆንስላው ተጨማሪ የደኅንነት ጥበቃ ኃይል ያስፈልገው እንደነበረ ፕሬዚዳንት ኦባማ እንዳልተነገራቸው ባይደን ገልፀዋል፡፡

“በኢራን የኒኩሌር መርኃግብር ላይ የኦባማ አስተዳደር ‘ተዓማኒነት የጎደለው’ በመሆኑ ምክንያት እስላማዊቱ ሪፐብሊክ ‘አጉራ ዘለል’ ወይም ‘ማንአለብኝ ባይ’ ሆናለች” ሲሉ ሚስተር ራያን ተችተዋል፡፡

ባይደን ግን ዩናይትድ ስቴትስ እጅግ የተጠናከሩና አቅም የሚያሣጡ ወይም አሽመድማጅ ማዕቀቦችን በኢራን ላይ መጣሏን ተናግረው የራያንን ክሥ ውድቅ አድርገዋል፡፡

የሐሙስ ምሽቱ የምክትል ፕሬዚዳንትነት ዕጩዎቹ ክርክር የተካሄደው ባለፈው ሣምንት ከተደረገው የፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማና የዕጩ ፕሬዚዳንቱ ሚት ራምኒ ክርክር ወዲህ የሪፐብሊካኑ ዕጩ የመራጭ ድጋፍ ቁጥር እያሻቀበ መምጣቱ እየተነገረ ባለበት ወቅት ነው፡፡

የ69 ዓመቱ ዴሞክራቱ ጆ ባይደን ከ36 ዓመታት ልምዳቸው ጋር እጅግ የተካኑ ፖለቲከኛና የተሣለጡ ተሟጋች እንደሆኑ በስፋት ይታወቅላቸዋል፡፡ የ42 ዓመት ዕድሜው የዊስከንሰኑ እንደራሴ የሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጩ ምክትል ፕሬዚዳንት ፖል ራያን ደግሞ ከወግ አጥባቂዎቹ ሪፐብሊካን መካከል እየተነሱ እንዳሉ ኮከብ የሚቆጠሩ ሰው ናቸው፡፡


በምክትል ፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎቹ መካከል የተካሄደው እሰጥ አገባ ይህ አንድና ብቸኛው ሲሆን ፕሬዚዳታዊ ዕጩዎቹ ግን ከሚቀሯቸው ሁለት ክርክሮች አንደኛውን የፊታችን ማክሰኞ፤ ጥቅምት 6 ኒው ዮርክ ውስጥ በስብሰባ አዳራሽ ከታዳሚዎች በሚቀርቡላቸው ጥያቄዎችና በሁለገብ ርዕሶች ላይ ያካሂዳሉ፡፡
XS
SM
MD
LG