በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የኢትዮ-አሜሪካ ግንኙነት በዚህ በምርጫ አመት እንዴት ይገመገማል?


ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ
ፕሬዝደንት ባራክ ኦባማ

"ኢትዮጵያ ተግባሯን ታስተካክል ዘንድ ከሞራል ጫና በላይ አንዳች ኃይል ማሣረፍ ለዩናይትድ ስቴትስ ከባድ ይሆንባታል" ኢቭ ሣንድበርግ

በ1997 ዓ.ም በኢትዮጵያ የደመቀ የምረጡኝ ዘመቻ ውስጥ እንዲያ የበረታ ፉክክር ሲደረግ በዴሞክራሲ ገፅታዋ ለይ የተሃድሶ ነፋስ ያድራል ሲሉ ተስፋ የጣሉ ብዙ አሜሪካዊያን የዴሞክራሲ ተሟጋቾች ነበሩ፡፡ የተቃዋሚው ጎራ መሪዎችም እጅግ የበዙ ደጋፊዎቻቸውን ደጋግመው ወደ አደባባይ ማውጣት ችለው ነበር፡፡

ምርጫው ተጠናቅቆ ውጤት ሲወጣ ገዥው ፓርቲ በሰፋ አብላጫ ማሸነፉ ተነገረ፤ ተቃዋሚዎቹም 'ምርጫው ተጭበርብሯል' ብለው እሮሮ ሲያሰሙ ደጋፊዎቻቸው ዋና ዋና በሚባሉ ከተሞች ወደ ጎዳና ወጡ፡፡ ከመሃላቸው ወደ 200 የሚጠጋ ሰው በወቅቱ በተቀሰቀው ግጭት ውስጥ የጥይት ሰለባ ሆነ፡፡ ብዙዎች፤ የተቃዋሚ መሪዎችም፣ በምርጫው ያሸነፉም ሳይቀሩ በየእሥር ቤቱ ታጎሩ፡፡

ያ ነገር ከሆነ እነሆ አምስት ዓመት ሆነ፡፡ ዛሬ ታዲያ የውጭ የምርጫ ተንታኞች የፊታችን ዕሁዱን ምርጫ በከፋ ጥርጣሬ እያዩት ነው፡፡ 'ይህ ምርጫ ፍትሐዊ ይሆናል ማለት መዘባበት ነው' ሲሉ ከወዲሁ ይናገራሉ፡፡

ገዥው ፓርቲ መገናኛ ብዙኃኑን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን፣ በአሠርት የሚቆጠሩ የተቃዋሚ መሪዎችና ጋዜጠኞች ዘብጥያ መውረዳቸውንና ገለልተኛ የሆኑ የምርጫ ታዛቢዎች አለመኖራቸውን ጭምር እየዘረዘሩ የምርጫው ዝግጅት እራሱ በችግር የተዋጠ መሆኑን ታዛቢዎች ይጠቋቁማሉ፡፡ የአሜሪካ የተወካዮች ምክር ቤትም ብርቱ ወቀሣ እያሰማ መሆኑ ይወራል፡፡ ብዙ ቁጥር ያላቸው እንደራሴዎች 'የኢትዮጵያ መንግሥት እያደር አምባገነን ሆኗል' እያሉ እያሳሰቡ ነው፡፡

በቅርቡ ለኢትዮጵያ የተላኩት የአሜሪካ አምባሣደር ዶናልድ ቡዝ በዚያች ሃገር ዴሞክራሲ እንዲጠናከር፣ ሰብዓዊ መብቶችም እንዲከበሩ ለማስቻል እንደሚጥሩ ቃል መግባታቸውን የኦበርሊን ኮሌጅ የፖሊሲ መምህር ኢቭ ሣንድበርግ ተናግረዋል፡፡

"ይሁን እንጂ - ይላሉ ፕሮፌሰር ሣንድበርግ በመቀጠል - ኢትዮጵያዊያኑ ከቀደሙት አምባሣደሮችም እንዲህ ዓይነቶቹን ቃላት ሰምተዋል፡፡ አሁን ጥያቄው ቡዝ እውን አቅም አግኝተው የኢትዮጵያ መንግሥት ዴሞክራሲና ሰብዓዊ መብቶችን ያከብር ዘንድ አንዳች ተግባር ማከናወን ይችላሉ ወይ? ነው፡፡"

የአሜሪካ መንግሥት ኢትዮጵያ በዴሞክራሲ ጎዳና ወደፊት እንድትራመድ ለማድረግ ምን ያህል መጓዝ ወይም መግፋት እንደሚችል ግራ የተጋባ መንታ መንገድ ላይ ቆሟል፡፡ ኢትዮጵያ እኮ በጣም አስፈላጊ ሸሪክ ነች - ይላሉ በአንድ ወቅት ኢትዮጵያ ውስጥ የፖለቲካ አማካሪ ሆነው የሠሩት እኒሁ ፕሮፌሰር ኢቭ ሣንድበርግ፡፡

"በአንድ በኩል - አሉ ሣንድበርግ - በምዕራቡ ዐይን ኢትዮጵያ ከአጋንንቱ ብዙም ያልገነነውን የሶማሊያን መንግሥት አቋቁማለች፤ እየጠበቀችውም ነው፡፡ በዚህም በብዙ ኃላፊነት ተሸክማለች፡፡ ምክንያቱም ያንን መንግሥት የሚቃወመው'ኮ በአልቃይዳ ሠልፍ ውስጥ የቆመ አማፂ ቡድን ነው፡፡ ኢትዮጵያ እንደአስፈላጊ ሸሪክ የምትታይበት ሌላው ጉዳይ በቀንዱ አካባቢ ምን እየተከናወነ እንደሆነ ለማወቅ በብዙ የምንጠቀመው የእነርሱን የስለላ መዋቅር ነው፡፡ ታዲያ በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያዊያኑ እኛ እንደምንፈልጋቸው ያውቃሉ፡፡"

ከዚህ የፕሮፌሰር ሣንድበርግ አባባል ጋር በቅርቡ ኢትዮጵያ በሚገኘው የአሜሪካ ኤምባሲ የሚሲዮኑ ምክትል ኃላፊ የነበሩት ቶማስ ሃልም ይስማማሉ፡፡

'ኢትዮጵያ ቁልፍ የሆነች መልክዓ ምድራዊና ፖለቲካዊ ሥፍራ ነች' የሚሉት ሃል በዚያ ላይ የአፍሪካ ኅብረት ዋና ፅ/ቤትም የሚገኘው በዚያው እንደሆነ ያስታውሱናል፡፡ "በዚህ ምክንያት ኢትዮጵያ ተግባሯን ታስተካክል ዘንድ ከሞራል ጫና በላይ አንዳች ኃይል ማሣረፍ ለዩናይትድ ስቴትስ ከባድ ይሆንባታል፡፡" ብለዋል ዲፕሎማቱና አሁን በሣይመንስ ኮሌጅ የዓለምአቀፍ ግንኙነቶች ፕሮፌሰር ቶማስ ሃል፡፡

ፕሮፌሰር ሃል እንደሚሉት አሜሪካ በአፍሪካ ውስጥ ያሏት ተፎካካሪ ጥቅሞች መንግሥቷ የበረታ ጫና እንዳያሣድርም መሰናክል ይሆኑበታል፡፡

"የንግድ ግንኙነቶቻችን በመጠን አንፃር ሲታይ እምብዛም አይደሉም፡፡" ይላሉ ሃል፤ የገበያ ግንኙነቱን በንፅፅር ሲያስቀምጡም " ቻይናዊያኑ፣ ሕንዳዊያኑና ሣዑዲያኑ በኢትዮጵያ ውስጥ እየሠሩ ካሉት ጋር ሰነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ ብዙው ለሃገሪቱ የምናደርገው ሰብዓዊ ልገሣ ነው፤ የምግብ፣ ፀረ-ኤችአይቪ/ኤድስን የመሣሣሰሉ..." ብለዋል፡፡

የጆርጅ ሜሰን ዩኒቨርሲቲው ፕሮፌሰር ቴሬንስ ሊዮንስ ግን የኦባማ አስተዳደር ግንኙነቶቹን የቡሽ ከነበረበት ዓይነት ለመለወጥ እየጣረ መሆኑን ይጠቁማሉ፡፡

ሊዮንስ እንዲህ ይላሉ፡- "ባለፈው አስተዳደር ወቅት ዩናይትድ ስቴትስ ከኢትዮጵያ ጋር ለነበሯት ግንኙነቶች የፀጥታ ሥጋቶቿና ፀረ-ሽብር ጉዳዮች ዋነኛ ሚዛን ነበሩ፡፡ አሁን ግን እኔ እንደማስበው አስተዳደሩ ይህንን ግንኙነት እደገና እየፈተሸ ነው፡፡ ምንም እንኳ የፀጥታው ጉዳይ ባለበት ቢቀጥልም ዋናው ግን ዴሞክራሲ፣ ሰብዓዊ መብቶችና ከእነዚህ ጋር የተያያዙ ሌሎች ጉዳዮች ናቸው፡፡"

ሊዮንስ እንደሚሉት ግንኙነቱን ለመለወጥ አሥር ዓመትና ከዚያም በላይ ሊጠይቅ ይችላል፡፡ በእርሣቸው እምነት 'የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ከአዳዲሶቹ የኢትዮጵያ ገዥ ፓርቲ ባለሥልጣናት ጋር መሥራት ይኖርባቸዋል፡፡'

XS
SM
MD
LG