በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዴሞክራቲክ ፓርቲው ዕጩ፣ ፕሬዚዳንት ኦባማ ናቸው


ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ

ጥቅምት 27 / 2005 ዓ.ም ለሚካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ አጠቃላይ ምርጫ ዴሞክራቲክ ፓርቲው ለፕሬዚዳንትነት እንዲወዳደሩ ያጫቸው ባራክ ኦባማ ዕጩነታቸውን መቀበላቸውን በትናንት ምሽቱ የፓርቲያቸው ጉባዔ ላይ በይፋ አሣውቀዋል፡፡

please wait

No media source currently available

0:00 0:07:07 0:00
ቀጥተኛ መገናኛበመጭዎቹ የምረጡኝ ዘመቻቸው ሁለት የመጨረሻ ወራትም ደጋፊዎቻቸው አብረዋቸው እንዲቆሙ ጠይቀዋል፡፡ የቪኦኤ ብሔራዊ ዘጋቢ ጉባዔው ከተካሄደበት ሻርሎት ካሮላይና ያስተላለፈው ሪፖርት አለ፤

እስከአሁን ካደረጓቸው የምረጡኝ ዘመቻ ቅስቀሣዎቻቸው የትናንቱ የባራክ ኦባማ ንግግር እጅግ የጎላው ነበር፡፡

ለሁለተኛ የዋይት ኃውስ ዘመን የደጋፊዎቻቸውን ድምፅ ለማግኘት ያደረጉት የሃገሪቱን ምጣኔ ኃብት ገፅታ ወደ ተሻለ አቅጣጫ ማዞር መቻላቸውን ለማሣመን ያደረጉት ንግግራቸው ባልተቋረጠ የጉባዔው ተሣታፊዎች ጭብጨባና አድናቆት የታጀበ ነበር፡፡

“አሁን ችግሮቻችን የሚፈቱ ናቸው፤ ፈተናዎቻችን ልንጋፈጣቸው፤ ልናሸንፋቸው የምንችላቸው ናቸው፡፡ መንገዳችን አስቸጋሪ ሊሆን ይችላል፤ የሚያደርሰን ግን ወደተሻለ ሥፍራ ነው፡፡ የምጠይቃችሁም ያንን መድረሻ እንድትመርጡ ነው፡፡” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ፡፡

የዘንድሮው ምርጫ አሜሪካዊያን በምጣኔ ኃብት፣ በታክስ፣ በኢነርጂ፣ እንዲሁም በጦርነትና ሠላም ጉዳዮች ላይ በትውልድ የቀረበላቸው፤ በእርሣቸውና በተቀናቃኛቸው ሪፐብሊካኑ ሚት ራምኒ መካከል ያለ እጅግ የጠራ ምርጫ መሆኑን ሚስተር ኦባማ አመልክተዋል፡፡

የእርሣቸው ፖሊሲዎች ለከበርቴ አሜሪካዊያ ከቆመው የሪፐብሊካን መንገድ ይልቅ መካከለኛ ገቢ ያለውን አሜሪካዊ የሚያጠናክሩና ብዛቱንም የሚያሠፉ መሆናቸውን ለማስጨበጥ ሞክረዋል፡፡

ኦባማ አክለውም በውጭ ፖሊሲ ላይ አከናውኛለሁ የሚሉትን ተግባር የኢራቅን ጦርነት ማቆማቸውን፣ ጦራቸውን ከአፍጋኒስታን ለማውጣት ቀን መቁረጣቸውንና ኦሣማ ቢን ላደንን የገደለውን ልዩ ኃይል ተልዕኮ ማሣካታቸውን በመዘርዘር ተናግረዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በመጨረሻም አሜሪካዊያን ከፓርቲ ልዩነት ይልቅ ለብሔራዊ አንድነት ያደላ ድጋፍ እንዲሰጧቸው በመጠየቅ ነው ንግግራቸውን የቋጩት፡፡ “እያንዳንዱ ፍትሐዊ ድርሻውን በሚያገኝባት፣ - አሉ ኦባማ - ፍትሐዊ ድርሻውን በሚያበረክትባት፣ ሁሉም በአንድና አንድ ደንብ በሚመራባት ሃገር የምታምኑ ከሆነ በመጭው ምርጫ ድምፅ እንድትሰጡ እጠይቃለሁ፡፡”

ከፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ በፊት የተናገሩት ምክትላቸው ጆ ባይደን የተቀናቃኞቻቸው ሪፐብሊካን ዕጩዎች ሚት ራምኒ እና ፖል ራያን ዋነኛ ተቺ ናቸው ነው የሚባለው፡፡

ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ኦሣማ ቢን ላደንን ላስወገደው ተልዕኮ ትዕዛዝ የሰጡበትና የአሜሪካን የመኪና ኢንዱስትሪ ከሞት ለማትረፍ የወሰኑበት አቋሞቻቸው ሰውዬው ምን ያህል ጀግና እንደሆኑ ያሣያል ብለዋል - ምክትል ፕሬዚዳንት ባይደን፡፡ ፕሬዚዳንቱ አራት ተጨማሪ ዓመታት የሚገቧቸው መሆኑን ቅልብጭና ቁልጭ አድርገው ነው ያስረገጡት፡፡ “አሁን በኩራት የምንናገረው ባለፉት ስድስት ወራት ስናገር የሰማችሁኝን ነው፡፡ ኦሣማ ቢን ላደን ሞቷል፤ ጄነራል ሞተርስ ድኗል፡፡”

የራምኒ ዘመቻ ቡድን ባወጣው መግለጫ ፕሬዚዳንቱ ባለፉ አራት ዓመታት ተፈትነው ያልሠሩ ተመሣሣይ ፖሊስዎችን ለማራመድ ነው ድጋፍ እየጠየቁ ያሉት ብለዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ የተናገሩበት የጉባዔው የሦስት ቀናት ጉዞ ማብቂያ የጉባዔ መድረክ ምርጫው እስኪካሄድ ላለው ለመጭው የሁለት ወራት ጊዜ በብዙ ያነቃቃቸውና ጥንካሬን የሰጣቸው መሆኑን ቁጥራቸው የበዛ የዴሞክራቲክ ፓርቲው ልዑካን አመልክተዋል፡፡

የሕዝብ አስተያየት ቅኝቶች እንደሚጠቁሙት ሁለቱም ወገኖች ያላቸው የመመረጥ ዕድል እጅግ የተቀራረበ መሆኑን ያሣያሉ፡፡

ሁለቱም ቅስቀሣዎቻቸውን አጠናክረው ቀጥለዋል፡፡
XS
SM
MD
LG