በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሦሪያ ጉዳይ አሜሪካ ለጥቃት ዝግጁ ነች፤ እንግሊዝና ጀርመን ወጥተዋል


“ይህ ጥቃት ዓለምን የሚፈትን ነው” - ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ
“ይህ ጥቃት ዓለምን የሚፈትን ነው” - ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኬሪ ፕሬዚዳንት አሳድን “ነፍሰ ገዳይ” ብለው ጠሯቸው፡፡ የሦሪያ መንግሥት “የሚባለውን የኬሚካል ጥቃት አልፈፀምኩም” ይላል፡፡





የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ

please wait

No media source currently available

0:00 0:08:18 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

በሦሪያ ላይ ይወስዳሉ ተብሎ ለሚጠበቅ እርምጃ ገና ውሣኔ ላይ አለመድረሳቸውን ያስታወቁት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ ሦሪያ እንደማታዘምት በድጋሚ አረጋግጠዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ ዛሬ - ዓርብ ማምሻውን በሰጡት መግለጫ የሚወስዱት ወታደራዊ እርምጃ እጅግ ለተወሰነ ጊዜና በተወሰኑ ዒላማዎች ላይ የሚያተኩር እንደሚሆን አመልክተው ከአየር ድብደባ ሃሣባቸው በተጨማሪ ሌሎችም አማራጮችን እየፈተሹ መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ “ይህ ጥቃት ዓለምን የሚፈትን ነው” ብለው የአየር ድብደባ ብቻውንም መፍትሔ ያመጣል ብለው እንደማያምኑ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የመንግሥታቸው ፍላጎት ዲፕሎማሲያዊና ፖለቲካዊ መፍትሔ ማግኘት እንደሆነ የገለፁት የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ ከፕሬዚዳንቱ ጥቂት ቀደም ብለው ባደረጉት ንግግር ዓለም ዛሬ በሦሪያው መንግሥት ላይ የሚወስደው ማንኛውም ዓይነት ውሣኔ ትርጉም ያለውና ምንም እርምጃ አለመውሰድም የወደፊት አርአያነቱ የከፋ እንደሚሆን አሳስበዋል፡፡

“ፕሬዚዳንቱ ሊወስዱ የሚወስኑት እርምጃ የተወሰነና አምባገነኑ የመርዝ ጋዞችን በጭካኔና በማንአለብኝነት ጥቃት ላይ በማዋል ተግባራቸው ሳይጠየቁ አለመቅረታቸውን ለማረጋገጥ የሚወሰድ እንደሚሆን ግልፅ አድርገዋል፡፡” ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡

ሚኒስትሩ የሶሪያውን ፕሬዚዳንት “ነፍሰ ገዳዩ” ሲሉ ጠርተዋቸዋል፡፡
ምንም እንኳ ባሻር አል አሣድ “በራሣቸው ሕዝብ ላይ አድርሰውታል” ስለተባለው የኬሚካል መርዝ ጥቃት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መርማሪዎች የፍተሻና ክትትላቸውን ሪፖርት ይፋ ያደርጋሉ ተብሎ እየተጠበቀ ቢሆንም የኦባማ አስተዳደር ግን ማስረጃዎች አሉኝ እያለ ነው፡፡

ጆን ኬሪ ባደረጉት ንግግራቸው ባለፈው ነኀሴ 15/2005 ዓ.ም ማለዳ የአማፂያኑ ይዞታ በሆኑ የደማስቆ አካባቢዎች ላይ የተተኮሱ ሮኬቶች የመርዝ ጋዞችን አረሮች የጫኑ እንደነበሩ፤ መቼና ከየት እንደተተኮሱ፣ የት እንደወደቁና መቼ እንደወደቁ የቅኝትና የክትትል ሰዎቻቸው በትክክል እንደሚያውቁ ተናግረዋል፡፡

ምንም እንኳ የባሻር አል አሣድ መንግሥት ከዚያ በፊትም አነስ ባለ ሁኔታ የመርዝ ጋዞቹን በራሱ ሕዝብ ላይ መጠቀሙን ቢያውቁም በዚያ ጥቃት ግን 426 ሕፃናትን ጨምሮ 1429 ሰው መገደሉን አስታውቀዋል፡፡ እርዳታ ላይ የነበሩ ሃኪሞችና የሟቾቹ ቤተሰቦችም በተለያየ ደረጃ መጎዳታቸውን አመልክተዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ የተናገሩትን ግን “የእርሣቸው የቀድሞ አቻ ፕሬዚዳንት ቡሽ ኢራቅን ከመውረራቸው ጥቂት ቀደም ብሎ የተናገሩትን ዓይነት ፍፁም መሠረት የሌው ውሸት ነው” ሲል የሦሪያ መንግሥት በሚቆጣጠረው ቴሌቪዥን ጣቢያው መናገሩ ተዘግቧል፡፡
የመከላከያ ሚኒስትር ቻክ ሄግል
የመከላከያ ሚኒስትር ቻክ ሄግል

ሰሞኑን መግለጫ የሰጡት የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ቻክ ሄግልም ጦራቸው በተጠንቀቅ ቆሞ የጠቅላይ አዛዡን የባራክ ኦባማን ትዕዛዝ ብቻ እየጠበቀ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

የዋሽንግተኑን የቅርብ ምሥራቅ ፖሊሲዎች ኢንስቲትዩቱን ጄፍሪ ዋይትን የመሣሰሉ ታዛቢዎች ይህ ሁኔታ የሚሸትተው ጦርነት አይቀሬ መሆኑን ነው ይላሉ፡፡

ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት የሚጠብቁት ውሣኔ አስኳል “የሃገራችንንና የዓለምን ደኅንነት አደጋ ላይ የሚጥሉት ክፉ መሣሪያዎች ከእንግዲህ በምስኪን ሕዝቦች ላይ እንዳይጣሉ የሚያረጋግጥ” መሆን እንደሚኖርበት አሳስበዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ኬሪ፡፡

ወታደራዊ ጥቃት ሊያደርሱ እንደሚችሉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ከትናንት በስተያ - ረቡዕ ከተናገሩ ወዲህ የአየር ድብደባው የሚፈፀምበት ጊዜ ጭምጭምታ እየተስፋፋ መጥቷል፡፡

ትዕዛዙ መቼ ቢተላለፍ እንደሚሻል የኦባማ አስተዳደር እንዲወስን እየተጠበቀ ቢሆንም ፕሬዚዳንቱም በዛሬው ንግግራቸው ስለጊዜው የሰጡት ፍንጭ የለም፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካምረንን
ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካምረንን

በሌላ በኩል ደግሞ ምንም እንኳ ዘመቻው “የአሜሪካ ዘመቻ” እንዲሆን ዋሽንግተን ፍላጎት ባየኖራትም እንግሊዝ በሦሪያ ጉዳይ እራሷን ከጦር ተግባር እንድታርቅ ፓርላማዋ ወስኗል፡፡ ይህ ውሣኔም ጠቅላይ ሚኒስትሯን ዴቪድ ካምረንን አሣዝኗል፡፡

ዩናይትድ ስቴቴስ እንደአውራ አጋሮች ከምትቆጥራቸው የአውሮፓ ሃገሮች አንዷ ጀርመንም ከወታደራዊ ጥቃት ሃሣብ እራሷን በማራቋ አሜሪካ የምትፈልገው ግንባር የመፍጠር ሃሣብ የሚሣካ እንደማይመስል ታዛቢዎች እየተናገሩ ነው፡፡

ለዝርዝር መረጃ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡
XS
SM
MD
LG