በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢየሩሣሌም፤ አሜሪካ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና የኢትዮጵያ ድምፆች


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ

ኢትዮጵያ የትረምፕ አስተዳደር በኢየሩሣሌም ላይ ይፋ ያደረገውን አቋም ከሚያወግዙ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት አባላትና የመንግሥታቱ ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ታደሚዎችም ጎን ቆማለች።

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትረምፕ ኢየሩሣሌም የእሥራኤል ዋና ከተማ ነች፤ ኤምባሲዬንም ከቴል አቪቭ ወደዚያው ለማዞር ወስኛለሁ ካሉ ወዲህ ዓለም በተለያዩ ጎራዎች ቆሞ እየተሟገተ ይገኛል። መካከለኛው ምሥራቅም ወደ አዲስ ውጥረትና የተቃውሞ ትርምስ ገብቶ ሰንብቷል።

ሚስተር ትረምፕና ደጋፊዎቻቸው እሥራኤል ዋና ከተማዋ የት እንደሚሆን የመደንገግ መብት ያላት ሉዓላዊት ሃገር ነች፤ ሆኖም ውሣኔዬ ዛሬ መሬት ላይ ያሉ ሁኔታዎችን አይለውጥም ሲሉ በአንፃራቸው የቆሙ ደግሞ ጉዳዩ በእሥራኤላዊያኑና በፍልስጥዔማዊያኑ በሁለቱ ብቻ የሚፈታ በመፍትኄዎች መጨረሻ ላይ ሊወሰን የሚገባው ጉዳይ ነው እያሉ ናቸው።

የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ድምፅ የሰጠበት ስብሰባ
የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ድምፅ የሰጠበት ስብሰባ

ጉዳዩን ወደ ጠረጴዛ ያወጣው የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ አሥራ አራት አባላት በግብፅ ጥያቄ መሠረት መክሮ የሚስተር ትረምፕን አቋም እንደሚቃወሙ ቢያሳውቁም አሜሪካ ድምፅን በአንድ ድምጿ የመጣል ሥልጣን ወይም አቅም ካላቸው አምስት ሃገሮች አንዷ ነችና ጣለችው።

ቀጥሎም ለጠቅላላ ጉባዔው በቱርክ መንግሥት የቀረበው ረቂቅ 128 ለዘጠኝ በሆነ ድምፅ የድርጅቱ አባላት የአሜሪካን አቋም አወገዙ።

የጠቅላላ ጉባዔው የድምፅ አሰላለፍ
የጠቅላላ ጉባዔው የድምፅ አሰላለፍ

ፕሬዚዳንት ትረምፕ እና በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የአሜሪካ አምባሣደር ኒኪ ሄሊ የሚቃወሟቸው ሃገሮች በወደፊት ግንኙነቶቻቸው ላይ ጠባሳ እንደሚያኖሩ፣ እንዲያውም አሜሪካ በምትሰጣቸው እርዳታዎችና ድጋፎች ላይ የቅጣት እጆቻቸውን ሊያሣርፉ እንደሚችሉ እየዛቱ ሲያስጠነቅቁ ተሰምተዋል።

በተመድ የዩኤስ አምባሳደር ኒኪ ሄሊ ለጠቅላላ ጉባዔው ንግግር ሲያደርጉ
በተመድ የዩኤስ አምባሳደር ኒኪ ሄሊ ለጠቅላላ ጉባዔው ንግግር ሲያደርጉ

ይህንን የድምፅ አሰጣጥ እንዲተነትኑልን ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉን ጠይቀናል። ፕሮፌሰር ብሩክ ትንታኔያቸውን የሰጡን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ታዳሚዎች በአሜሪካ አቋም ላይ ያላቸውን ተቃውሞ በሰፋ የድምፅ ልዩነት እንዳሳወቁ ነበር። ቃለ-ምልልሱን ካደረግን ወዲህ ሥጋታቸው ዕውን ሆኖ ዩናይትድ ስቴትስ ለድርጅቱ በጀት ከምትሰጠው ዓመታዊ መዋጮዋ ከሲሦ በላይ የሚሆን ገንዘብ መቁረጧን ትናንት አሳውቃለች።

ዶ/ር ብሩክ በኦሃዮ ዩኒቨርሲቲና በኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ፣ እንዲሁም በስክሪፕስ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት የፖለቲካ ሣይንስ ፕሮፌሰር ናቸው። ዋሺንግተን ላይ የኢትዮጵያ ምክትል አምባሳደር ሆነው አገልግለዋል። በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሣይንስና የባሕል ድርጅት - ዩኔስኮ ኢትዮጵያን ወክለው ፓሪስ ላይ ሠርተዋል። አሁንም ባሉባቸው ዩኒቨርሲቲዎች በተባበሩት መንግሥታት ድርጅትና በድርጅቱ የሰላም ጥበቃ ተልዕኮዎች ላይ የተለያዩ ኮርሶችን በከፍተኛ ደረጃ ይሰጣሉ። ቀደም ሲልም በዋሺንግተን ዲሲው ጆርጅ ዋሺንግተን ዩኒቨርሲቲ በአፍሪካ አካባቢያዊ ፀጥታ ላይ አስተምረዋል።

ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ
ፕሮፌሰር ብሩክ ኃይሉ

ፕሮፌሰር ብሩክ ቀደም ሲልም በዓለምአቀፍ ግንኙነቶችና የዩናይትድ ስቴትስን ሁኔታዎች ጨምሮ በተለያዩ የፖለቲካ ጉዳዮች፣ እንዲሁም በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አመራር፣ ሕልውና፣ አስፈላጊነትና ተልዕኮዎች ላይም ተከታታይ ትንታኔዎችን ሲሰጡን ቆይተዋል።

ለሙሉው ቃለ-ምልልስ የተያያዘውን የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG