በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለቀንዱ ረሃብ ዓለምአቀፍ ምላሽ


የዘንድሮው የምሥራቅ አፍሪካ ረሃብ ገፅታ
የዘንድሮው የምሥራቅ አፍሪካ ረሃብ ገፅታ

ለዘንድሮው የአፍሪካ ቀንድ የበረታ ረሃብ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ እየተጣደፈ መሆኑን የዩናዩይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት ከፍተኛ ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡

ባለሥልጣናቱ ትናንት በውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መሰሉ ባለፉት ስድሣ ዓመታት ባልታየው በዚህ ድርቅ ሣቢያ በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ከ 11 ሚሊየን በላይ ሰው አፋጣኝ የሕይወት አድን እርዳታ እንደሚያስፈልገው አመልክተዋል፡፡

ጋዜጣዊ መግለጫውን የሰጡት በዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትር አምባሣደር ጆኒ ካርሰን፣ የመሥሪያ ቤቱ የሥነ-ሕዝብ፣ የስደተኞችና የፍልሰት ጉዳዮች ዋና ምክትል ረዳት ሚኒስትር ዶ/ር ሩበን ብሪጌቲ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የዓለምአቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤአይዲ) ምክትል ኃላፊ ዶናልድ ስታይንበርግ እና የኤጀንሲው የዴሞክራሲ፣ የግጭቶችና የሰብዓዊ ድጋፍ ረዳት ኃላፊ ናንሲ ሊንድበርግ ናቸው፡፡

የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ዕርዳታውን ለአካባቢው ለማድረስ ከዓለምአቀፍ የረድዔት ተቋማት ጋር በቅርበት እየሠራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱና የዓለምአቀፍ ተራድዖ ተቋሙ ከፍተኛ ኃላፊዎች ተናግረዋል፡፡

አምባሣደር ጆኒ ካርሰን በኢትዮጵያ ቢያንስ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን፣ በሶማሊያ በመቶ ሺሆች የሚቆጠሩ ወደ ኢትዮጵያና ወደ ኬንያ የገቡ ስደተኞችን ሳይጨምር ሦስት ሚሊየን፣ በኬንያ የሶማሊያ ስደተኞችን፣ የገጠር ከብት አርቢዎችንና በምግብ ዋጋ መናር የተጎዱ የከተሞች ነዋሪዎችን ጨምሮ 3 ነጥብ 5 ሚሊየን ሰው አፋጣኝና ነፍስ አድን ሰብዓዊ እርዳታ እንደሚያስፈልገው ገልፀዋል፡፡

ምክትል ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ላይ ምሥራቅ አፍሪካን ካዳረሰው የድርቅ አደጋ የተለየች ወይም ያመለጠች ልትሆን አትችልም ብለው እንደሚገምቱ ያነሷት ኤርትራ መንግሥት ዝግ በመሆኑ ምክንያት ከዚያ መረጃ ማግኘት አለመቻሉን አመልክተዋል፡፡

"ጨቋኙ አገዛዝ የራሱን ሕዝብ ሰብዓዊ ድጋፍ ፍላጎት መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ባልሆነባት ኤርትራ የበዛ ቁጥር ያላቸው እርዳታ የሚፈልጉ ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ነፃ የመረጃ ልውውጥ ሰዎች አደጋን ቀድመው ለማስወገድ ምርጫዎቻቸውን እንዲወስዱ የሚያስችላቸው መሣሪያ ነው፡፡ የኤርትራ መንግሥት በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን የረሃብና የምግብ እጥረት ችግር ለመጋፈጥ እንጂቻል ከተባበሩት መንግሥታት ተቋማትና ከዓለምአቀፍ ድርጅቶች ጋር እንዲተባበር ጥሪ እናቀርባለን" ብለዋል አምባሣደር ጆኒ ካርሰን""

ለዚህ የአምባሣደር ጆኒ ካርሰን ክሥ መልስ የሰጡት ኤርትራው የማስታወቂያ ሚኒስትር አቶ አሊ አብዱ እንዲህ አሉ፡-

"በመጀመሪያ ይህንን ብሶታቸውን ሰበብ አድርገው በኤርትራ ዝናብ እንዳይጥል ማዕቀብ መጣል እንደማይችሉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ እነዚህ ሰዎች ምንም ነገር ስላልጠየቃቸው ስለኤርትራ ሕዝብ ስለምን ይጨነቃሉ? የኤርትራ ሕዝብ ሌሎች እንዲመግቡት ሳይጠይቅ ስለለምን ምግብ እንስጥህ እያሉ ያስጨንቁታል? አምላክ ይመስገን በቂ አለን፡፡ የቤት ሥራችንን ሠርተናል፡፡ የምግብ ዋስትና ስትራተጂያችንን አረጋግጠናል፡፡ የምግብ ክምችት የቤት ሥራችንን ሠርተናል፡፡ ሰዎችን መመገብ ካለባቸውና ካልመገብን ብለው ብዙ የሚያስቸግሩ ከሆነ በልመና ወደ ተካኑትና የምግብ እርዳታን እንደሙያ ወደያዙት እንደኢትዮጵያ ወዳሉ ሃገሮች ይሂዱ፡፡"

የአፍሪካ ቀንድን ሰብዓዊ ቀውስ ካባባሱት ሁኔታዎች መካከል ወደ ኢትዮጵያና ወደኬንያ የሚጎርፉት የሶማሊያ ስደተኞች መሆናቸውን በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት አጠንክረው የተናገሩት የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ምክትል ሚኒስትር አምባሣደር ጆኒ ካርሰን ለሶማሊያ ለራሷ ሰብዓዊ ቀውስና ለረሃቡም መመርታት ምክንያት የሆኑት የተፈጥሮው ክስተት፣ በአግባቡ የሚሠራ ማዕከላዊ መንግሥት አለመኖርና ፀረ-ምዕራብ አቋም ያለውና የሽብር ቡድን ነው ያሉት አልሻባብ ካለፈው ዓመት ጥር ወር ጀምሮ የውጭ የረድዔት ድርጅቶት በቁጥጥሩ ሥር ባሉ አካባቢዎች እንዳይንቀሣቀሱ በመከልከሉ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አልሻባብ የስትራተጂ ለውጥ ማድረጉን ሚስተር ካርሰን ሲናገሩ "በቅርቡ ባገኘናቸው ሪፖርቶች አልሻባብ በቁጥጥሩ ሥር ወዳሉ አካባቢዎች ዓለምአቀፉ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲገባ መፍቀዱን ሰምተናል፡፡ ይህንን በተመለከተ አልሻባብ በፖሊሲዎቹ ላይ እውነተኛ ለውጦችን አድርጎ እንደሆነና እኛና ሌሎችም በነፃነት መንቀሣቀስ እንችል እንደሆነ፣ በሰብዓዊ አቅርቦቶች ላይም ታክስ እንደማይጥል ለማረጋገጥ ከዓለምአቀፎቹ ድርጅቶች ጋር እየተመካከርን ነው" ብለዋል፡፡

ይህ ችግር በአፍሪካ ቀንድ አካባቢ ሲደርስ የመጀመሪያ አለመሆኑን፣ በመጭው ሣምንት ወይም በመጭው ወርም ይፈታል ተብሎ የሚጠበቅ አለመሆኑን ባለሥልጣናቱ ተናግረዋል፡፡

ከአፋጣኙ እርዳታ በተጨማሪ ግን ዘላቂ መፍትሔ ለመሻት ከአካባቢው መንግሥታት ጋር በቅርበት አብረው እንደሚሠሩ ሚስተር ካርሰን ሲገልፁ የወደፊቱ መርኃግብር የግብርና ምርታማነትን በማሣደግ፣ ከዝናብ ጠባቂ ግብርና በመውጣት፣ የተሻሉ የክምችት ዘዴዎችን በማስተዋወቅ፣ ዘመናዊ የአስተራረስ ዘዴዎችን ተግባራዊ በማድረግ፣ በመላው የአፍሪካ ቀንድ ሰዎች እጅግ ተለዋዋጭ ከሆኑት የአየር ሁኔታ አካሄዶች ጋር እንዲለማመድ ሣይንስና ቴክኖሎጂን ሥራ ላይ በማዋል ላይ የታለመ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በሕፃናት ላይ የሚታየው እጅግ አሣሣቢ የሆነና ከአጠቃላዩ ግማሽ በሚሆኑ ሕፃናት ላይ የሚስተዋለው አጣዳፊ የምግብ እጥረት ችግር የተሻለ ከመሆኑ በፊት እየተባባሰ የመሄድ አዝማሚያ እንደሚኖረው ባለፈው ሣምንት በኢትዮጵያ ዶሎ ኦዶ እና በኬንያ ዳዳብ ጉብኝት አድርገው የተመለሱት የስደተኞች ጉዳዮች ረዳት ሚኒስትሩ ዶ/ር ሩበን ብሪጌቲ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የዓለምአቀፍ ልማት ተቋሙ ዩኤስኤአይዲ ምክትል ኃላፊ ዶናልድ ስታይንበርግ ይህንን አሣዛኝ አደጋ ቀደም ሲልም ተንብየው የነበር በመሆኑ መሥሪያ ቤታቸው ካለፉት ሐምሌና ነሐሴ ወራት ጀምሮ ሲዘጋጅ እንደነበረ አመልክተዋል፡፡

በዩኤስኤአይዲ በሚደገፈው "ፊውስ ኔት" እየተባለ በሚጠራው የበረታ ረሃብ የቅድሚያ ማስጠንቀቂያ መረብ አማካይነት ያገኙትን ትንበያ በመመርኮዝ ባለፈው ነሐሴ ምግብና ሌሎችም አቅርቦቶችን በጅቡቲ፣ በደቡብ አፍሪካና በሌሎችም የአካባቢው ሃገሮች ማከማቸት መጀመራቸውን ገልፀዋል፡፡ በዚህም መሠረት ከጥቅምት ጀምሮ የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት 4 ነጥብ 4 ሚሊየን ለሚሆኑ ተጎጂዎች 348 ሺህ ሜትሪክ ቶንስ ምግብን ጨምሮ 383 ሚሊየን ዶላር የሚያወጡ አቅርቦቶችን እያደረሰ እንደሚገኝ ሚስተር ስታይንበርግ አስረድተዋል፡፡

የማኅበረሰብ አደጋን የመቋቋም ሥራዎች በተለያዩ ደረጃዎች መከናወናቸውና እንደምግብ ለሥራን በመሣሰሉ መርኃግብሮች ሰዉን በመሠረተ ልማትና የአገልግሎት ተቋማት ግንባታ ላይ ማሠማራት በመቻሉ በኢትዮጵያ ያለው የረሃብ ሁኔታ በ1995 ዓ.ም ታይቶ ከነበረው የ15 ሚሊየን የምግብ እርዳታ ፈላጊ ቁጥር በዚህኛው የድርቅ አደጋ ወደ 4 ነጥብ 5 ሚሊየን ለማውረድ መቻሉን የዩኤስአይዲ የዴሞክራሲ፣ የግጭቶችና የሰብዓዊ ድጋፍ ረዳታ ኃላፊዋ ናንሲ ሊንድበርግ ተናግረዋል፡፡

ዘገባውን ያዳምጡ፡፡

XS
SM
MD
LG