ስሎቫኪያ እና ሃንጋሪን ጨምሮ የምስራቅ አውሮፓ ሀገሮች በመጪው ክረምቱ ሲቃረብ የዩክሬን ስደተኞች ቁጥር ይጨምራል ብለው እየተጠባበቁ ናቸው።
ሩሲያ ባለፉት ወራት የዩክሬን የኤሌክትሪክ እና የማሞቂያ ኃይል ጣቢያዎችን ዒላማ አድርጋ ስትደበድብ ቆይታለች። በአካባቢው ቅዝቃዜው እጅግ የሚበረታ ሲሆን የዩክሬን ፕሬዚደንት ቮሎዶሚር ዜሌንስኪ ባሁኑ ወቅት ከአራት ሚሊዮን በላይ ህዝብ ኤሌክትሪክ ኃይል እንደሌለው ተናግረዋል።
የሆነ ሆኖ ሩሲያ ወረራዋን ለመቀጠል ወታደሮቿን ማዝመቷን እና ተጠባባቂ ጦሩን ለዘመቻ መጥራቷን ቀጥላለች። ባለፈው ወር የወደመውን የክራይሚያ ድልድይ እያደሰች ሲሆን የብሪታንያ የመከላከያ ሚኒስቴር በበኩሉ ዕድሳቱ አልቆ ሥራ ለመጀመር ወራት ሊወስድ እንደሚችል ገልጿል።
ሩስያ በተቆጠጠረቻቸው የዩክሬን አካባቢዎች ክሬምሊን የሰየማቸው የሲሜሪቭካ ከተማ ከንቲባ ከባድ ውጊያ እየተካሄደ ነው ማለታቸው ተጠቅሷል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ድርጅት ኔቶ አባል ሀገሮች መሪዎች በመጪው ሃምሌ አጋማሽ ሊቱዌኒያ ቪሊኒየስ ከተማ ጉባዔ እንደሚያካሂዱ አስታውቀዋል። ባለፈው ሰኔ ማድሪድ ላይ ተሰብስበው እንደነበር ይታወሳል።
የህብረቱ ዋና ጸሃፊ ዬንስ ስቶልትንበርግ እንዳሉት ጉባኤተኞቹ የድርጅቱን የመከላከያ ቅም ለማሳደግ መወሰድ ያለባቸውን ዕርምጃዎች እንዲሁም የመከላከያ ወጪ መጨመር እና ለዩክሬን የሚሰጠውን ድጋፍ መቀጠልን በሚመለከት ለመነጋገር ታቅዷል።