የሩሲያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በአውሮፓ ትልቁን የኒዩክሌር ማመንጫ የያዘችውንና የዩክሬን ግዛት የሆነችውን ዛፖሪዥዢያና ሌሎች ሦስት ግዛቶችን ወደ ሃገራቸው እንደሚጠቀልሉ ትናንት በህግ ላይ በመፈረም ካሳወቁ በኋላ፣ በዛፖሪዥዢያ ላይ በመኖሪያ ህንጻዎች ላይ ዛሬ በተፈጸመ ድብደባ ቢያንስ ሁለት ሰዎች ሳይሞቱ እንዳልቀረ ባለሥልጣናት ተናግረዋል።
የዛፖሪዥዢያ ሀገረ-ገዢ በቴሌግራም መተግበሪያ ባሰራጩት መልዕክት አምስት ሰዎች በፍርስራሹ ሥር ተጠምደዋል።
የዛፖሪዥዢያ ክልል በአብዛኛው በሩሲያ ቁጥጥር ስር ሲሆን፣ ከተማዋን ግን አሁንም ዩክሬን ትቆጣጠራለች።
በአውሮፓ ትልቁ የኒዩክሌር ማመንጫ በሚገኝበት ዛፖሪዥዢያ እየተካሄደ ያለው ድብደባ የኒዩክሌር አደጋ እንዳያስከትል ተሰግቷል።
የተመድ አቶሚክ ኃይል ኤጀንሲ ኃላፊ ራፋኤል ግሮሲ በዚህ ሳምንት ኪቭንና ሞስኮን እንደሚጎበኙ ታውቋል። “በኒዩክሌር ማመንጫው አካባቢ የደህንነት ቀጠና መፍጠር ከምንግዜውም በላይ አሁን አስፈላጊ ነው” ሲሉ ግሮሲ ዛሬ ተናግረዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በዛሬው የምሽት መልዕክታቸው ጦራቸው ሦስት ግዛቶችን መልሶ መቆጣጠሩን አስታውቀዋል። ሦስቱ ግዛቶች ሩሲያ ከድንበሯ ጋር መቀላቀሏን ባስታወቀጭው ኬርሶን ክልል የሚገኙ ናቸው።
ይህ በእንዲህ እንዳለ የዩናይትድ ስቴትስ ዓለም አቀፍ ልማት ድርጅት ኃላፊ የሆኑት ሰማንታ ፓወር ዛሬ በዩክሬን መዲና ኪየቭ ተገኝተዋል። ድርጅቱ እንዳለው ኃላፊዋ በዛ የሚገኙት ከመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ገበሬዎች፣ ጋዜጠኞች፣ ነጋዴዎችና ከኃይል ማመንጫ ሠራተኞች ጋር የዩክሬንን ህዝብ በተቀላጠፈ መንገድ መርዳት የሚቻልበትን መንገድ ለመመካከር ነው።
“ነፃነታቸውን ላለማስነካት ከጭካኔ ጥቃት ራሳቸውን የሚከላከሉበት፣ በኃይል የተያዙ መሬቶቻቸውን የሚያስለቅቁበት፣ ለቀዝቃዛው የበረዶ ወቅት የሚዘጋጁበት እንዲሁም ዲሞክራሲያዊ ተቋሞቻቸውንና የህግ የበላይነትን የሚያጠናክሩበት ይህ ወቅት፣ ለዩክሬናውያን ወሳኝ ወቅት ነው” ሲሉ ሳማንታ ፓወር በትዊተራቸው ጽፈዋል።