በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አሜሪካ ራሽያ ላይ ጠንካራ ማዕቀብ ጣለች


ዩናይትድ ስቴትስ የራሽያ ማዕቀብ ሰነድ ሽፋን
ዩናይትድ ስቴትስ የራሽያ ማዕቀብ ሰነድ ሽፋን

የባይደን አስተዳደር ትናንት ሀሙስ ባወጣው መግለጫ፣ ሩሲያ፣ በዩናይትድ ስቴትስ ትልቁን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂን የመረጃ መረብ በሚያስተዳድረው፣ የሶላርዊንድስ ድርጅት ላይ፣ የስለላና የጥቃት ዘመቻ በመፍጠር፣ እንዲሁም የ2020 ምርጫ ላይ ተጽእኖ ለማሳደር መሞከሯን ተከትሎ፣ ጠንካራ የኢኮኖሚ ማዕቀብ የተጣለባት መሆኑን አስታውቋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ትናንት ባወጣቸው መግለጫ፣ ሩሲያ፣ የሳይበር መረጃ መረብን በመጠላለፍ፣ የምርጫውን ሂደት ጣልቃ ገብታ በማደነቃቀፍና በሌሎች ጎጂ ድርጊቶቿ፣ የበረታ ቅጣት የተጣለባት መሆኑን አስታውቃለች፡፡

ፕሬዚዳንት ባይደን ለራሽያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ሳምንት መጀመሪያ ላይ ባደረጉላቸው የስልክ ልውውጥ፣ ይህንኑ ያሳወቅዋችው መሆኑም ተዘግቧል፡፡

ባይደን፣ በዚህ ዓመት በአውሮፓ በሚደረገው ስብሰባም፣ ፑቲን እንዲገኙ የጋበዝዋቸው መሆኑም ታውቋል፡፡

እንዲህ ብለዋል ባይደን

“በዩናይትድ ስቴትስ ከራሽያ ጋር ለመስራት ፍላጎቱ አላት፡፡ መኖርም ይገባዋል፣ ወደፊትም ይኖረናል፡፡ ራሽያ የዩናይትድ ስቴትስ ጥቅሞች መጉዳት ስትፈልግ ግን ምላሹን እንሰጣለን፡፡ ሁልጊዜም አገራችንን፣ ተቋሞቻችንን ሰዎቻችንንና አጋሮቻችንን ለመከላከል ደግሞ እንቆማለን፡፡”

ዩናይትድ ስቴትስ በ2020ው ፕሬዚዳንታዊው ምርጫ ጣልቃ በመግባት ዶናልድ ትራምፕ እንዲመረጡ ጥረት አድርጋለች ከተባለችው ሞስኮ ጋር በተያያዘ፣ 10 የሩሲያ ዲፕሎማቶችን ከአገሯ ያባረረች ሲሆን፣ 32 የሚደርሱ ተቋማትና ግለሰቦችም ላይ ማዕቀብ ጥላለች፡፡

አሜሪካ ራሽያ ላይ ጠንካራ ማዕቀብ ጣለች
please wait

No media source currently available

0:00 0:05:54 0:00

በተመሳሳይ መግለጫም የባይደን አስተዳደር ከራሽያ ጋር አብሮ ለመስራት እንደሚፈልግ አስታውቋል፡፡

ከአትላንቲክ ባሻገር የአዲስቱ አሜሪካ የደህንነት ፕሮግራም ዳይሬክተር፣ አንድሪያ ኬንዳል፣ አብሮ ስለ መስራቱና ስለ መገፋፋቱ ጉዳይ እንዲህ ይላሉ

“በድጋሚ ይህንን አብሮ የመስራትና የመገፋፋት ፍላጎት የተደባለቀበትን ግንኙነት እንመለከታለን፡፡ በተለይም ለሞስኮ እጅግ አስፈላጊ በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ ማበረታቻ ለመፍጠር ጥረት ሲደረግም እናያለን፡፡ ለምሳሌ ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር የሚደረግን ዘላቂና ስትራቴጂክ ግንኙነት የሩሲያው ፕሬዚዳንት በጣም ይፈልጉታል፡፡ ለምሳሌ እንደ ኢራንና አፍጋኒስታን ባሉ ንግግሮች ላይ ሩሲያም ከውይይቱ ጠረጴዛ ላይ እንድትጨመር ይፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ እነዚያን ሁለቱን አቀራረቦች በማጣመር ግንኙነቱን ጠባቂ የሆኑ ነገሮችን ማስቀመጥ የሚቻል ይመስለኛል፡፡“

ባለፈው ታህሳስ ወር፣ በአሜሪካ ፌደራል ተቋማት እና የንግድ ድርጅቶች ይፋ ለተደረገው፣ የሶላርዊንዱ የሳይበር ጥቃት፣ ዋሽንግተን ለመጀመሪያ ጊዜ፣ ሞስኮን በግልጽ ተጠያቂ አድርጋታለች፡፡

ከዊልሰን ማዕከል ሩሲያ የምትነዛውን የመረጃ ውዥንብር የሚያጠኑት ኒና ጃንኮዊችዝ እንዲህ ይላሉ

“በሶላርዊንድ በደረሰው ጥቃት ገና በደንብ ይፋ ያልተደረጉና ያልተደረሰባቸው ሌላ መግቢያዎች ወይም ለሌላ አደጋ የሚያጋልጡ ነገሮች ሊኖሩ ይችላሉ፡፡ ራሺያ እነዚያን ነገሮች የምትጠቀምባቸው ከሆነ፣ በሩሲያ የስለላ ተቋሞች ላይ ምናልባትም በሩሲያ መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናትና ቤተሰቦቻቸው ላይ፣ ያነጣጠረ ማዕቀብ ሊቀጥል ይችላል፡፡ ያ ደግሞ አሁንም ብዙዎቹ የማዕቀብ ጠበብቶችም የሚገፋፉት ይመስለኛል፡፡”

ያለፉት ማዕቀቦች ሞስኮን ሊያንበረክኩ አልቻሉም፡፡ አሁን ግን ባይደን ፣ ከቀዳሚ የአክስዮን ገበያ ላይ፣ በሩሲያ የመገበያያው ገንዘብ፣ ሩብልን በመጠቀም፣ የሩሲያን ቦንድ የሚገዙ የአሜሪካ የፋይናንስ ተቋማትን ለማግደ፣ ተጨማሪ ግፊት እያደረጉባቸው መሆኑ እየተሰማ ነው፡፡

ዋይት ሀውስ አስፈላጊ ከሆነ፣ በሁለተኛው የአክስዮን ገበያም የሚደረገውን ግብይት ማገድ እንደሚሻ ፍንጮችን ሰጥቷል፡፡

የአሜሪካ ባንኮች ከ2019 አንስቶ ከሩብል ውጭ በሆኑ የአክስዮን ገበያዎች የሩሲያን ቦንድ በመግዛት የንግድ ልውውጦችን እንዳያደርጉ ታግደዋል፡፡

የዋይት ሀውስ የፕሬስ ሴክረታሪ ጄን ሳኪ እንደሚከተለው ያስረዳሉ

“ይህ ማለት፣ 80 ከመቶ የሚሆነው የሩሲያ ሉዓላዊ እዳ፣ በተለይም በሩብል የሚፈጸመው አብዛኛው ግብይት፣ በማዕቀባችን የተካተተ አይደለም፡፡ አሁን ግን ወደዚህም ክፍል እየገባን ነው፡፡ ይሁን እንጂ ግን አሁንም ወደፊት ለመሄድ የሚያስችሉን ብዙ አማራጮች አሉን፡፡ “

በራሽያ የክሬሊምን ሰዎች ግን፣ የተባለውን ክስ በሙሉ ያስተባብላሉ፡፡ የራሽያ የውጭ ጉዳይ ምኒስትር ቃል አቀባይ፣ ማሪያ ዛኮሮቫ እንዲህ ይላሉ

“እንደዚህ ያለው ጠብ አጫሪነት ባህርይ በእርግጠኝነት አጸፋው ይመለስለታል፡፡ ለማዕቀቡ ምላሽ መሰጠቱ የማይቀር ነው፡፡”

ማዕቀቦቹ የመጡት ራሽያ ወታደሮችዋን በዩክሬን ድንበር አቅራቢያ ማከማቸት ስትጀምር ነው፡፡ በአካባቢው፣ በዩክሬን መንግሥትና ራሽያ በምትደግፋቸው ኃይሎች መካከል፣ ላለፉት ሰባት ዓመታት የቀጠሉ፣ ግጭትን የሚያባብሱ ነገሮች፣ አሁንም አሉ፡፡

የእምርጃው ሌላው ምክንያት፣ ራሽያ በአፍጋኒስታን የነበሩ የዩናይትድ ስቴትስና አጋሮችዋን የጦር ሰዎች ለማስገደል፣ ቅጥር ነፍስ ገዳዮችን አሰማርታለች የሚለውም ክስ፣ እንደሚገኝበት ተመልክቷል፡፡

(የዋይት ሐውስ ዘጋቢ ፓትሲ ውዳክስዋራ ካጠናቀረችው ዘገባ የተወሰደ)

XS
SM
MD
LG