አሜሪካዊያኑ ወታደሮች ከኒዠር የሚወጡበትን መንገድ ለማቀናጀት የሚካሄደው የዩናይትድ ስቴትስ እና የኒዠር ከፍተኛ ባለስልጣናት ውይይት ተጀምሯል፡፡ በዩናይትድ ስቴትስ የመከላከያ ሚንስቴር የልዩ እንቅስቃሴዎች እና የመለስተኛ ግጭቶች ጉዳይ ረዳት ሚንስትር ክሪስቶፈር ሜይር እና የጋራ ኃይሎች ዕድገት ዳይሬክተር ሌተናንት ጀነራል ዳቪን አንደርሰን ትናንት ረቡዕ እና ዛሬ ሀሙስ ኒያሜ ላይ ከአዲሱ የኒዠር መንግሥት አባላት ጋር እየተወያዩ መሆኑን ሁለት የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ለቪኦኤ ገልጸዋል፡፡
የኒዠር መንግሥት ትናንት በኤክስ የማሕበራዊ መገናኛ ገጹ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው ሁለቱ ከፍተኛ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣናት ከወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥቱ አባላት መካከል አንዱ ከሆኑት እና የመከላከያ ሚኒስትር ሆነው ከተሾሙት ሌተና ጀኔራል ሳሊፉ ሞዲ ጋር ተነጋግረዋል፡፡
የኒዠር ደህንነት ብሔራዊ ምክር ቤቱ አያይዞም ከዩናይትድ ስቴትስ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር ስብስባው የተጀመረው ኒዠር ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር ያላትን የወታደራዊ ሠፈር ስምምነት ካወገዘችው ከሁለት ወራት በኋላ መሆኑን ጠቅሶ የወታደሮች አወጣጥ በጊዜ ገደቡ መሰረት ደህንነታቸው ተጠብቆ ሥርዓት ባለው መንገድ እንዲከናወን የተቻለንን ሁሉ እናደርጋለን ብሏል፡፡
ኒዠር ውስጥ ወታደሮች ሲቪሎች እና የክንትራት ሠራተኞችን ጨምሮ ዘጠኝ መቶ የሚሆኑ የዩናይትድ ስቴትስ ወታደራዊ አባላት ያሉ መሆኑን ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁ የዩናይትድ ስቴትስ ባለስልጣን ለቪኦኤ ገልጸዋል፡፡ የሚበዙት የአሚሪካ ወታደራዊ አባላት የሚወጡበት አኳሃን አስከሚመቻችላቸው ድረስ ከምድብ ጊዜያቸው በላይ እዚያው ኒዠር መቆየታቸው ተመልክቷል፡፡
መድረክ / ፎረም