አሜሪካ፣ ከሁለት ሺሕ በላይ የሚኾኑ የሠራዊቷ አባላት በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ማዘዟን፣ የመከላከያ ሚኒስትር ሎይድ ኦስትን፣ ትላንት ረቡዕ አስታውቀዋል።
ፔንታጎን ለቪኦኤ እንደገለጸው፣ ፕሬዚዳንት ባይደን ወታደሮቹ እንዲንቀሳቀሱ ትዕዛዝ ካስተላለፉ፣ አሜሪካ በመካከለኛው ምሥራቅ ያላትን የአየር ኃይል፣ የሕክምና እና የአቅርቦት እንዲሁም የስለላ፣ የቅኝት እና የቁጥጥር መጠንና ዐቅም ታሳድጋለች።
አሜሪካ ወደ መካከለኛው ምሥራቅ የላከችው፣ ሌላ አንድ የአውሮፕላን ተሸካሚ መርከብ፣ በጉዞ ላይ ይገኛል። በተጨማሪነት የተላከው ዩኤስኤስ ድዋይት አይዘናወር፣ በምሥራቅ ሜዲትሬንያን በተጠንቀቅ ላይ ካለችው ዩኤሴኤስ ጀራልድ ፎርድ ጋራ ይገናኛል። ጀራልድ ፎርድ፣ የስድስት ወር ግዳጇን ያጠናቀቀች ቢኾንም፣ የመከላከያ ሚኒስትሩ ሎይድ ኦስትን ግዳጇን አራዝመዋል።
በእኒኽ የኀይል ተጠንቀቆች እና ንቅናቄዎች፣ አሜሪካ በቀጣናው ጡንቻዋን እያፍታታች እንደምትገኝ ተመልክቷል።
በሺሕ የሚቆጠሩና በምድርም በባሕርም የሠለጠኑ ልዩ ወታደሮች፣ በእስራኤል የውኃ ዳርቻ ይገኛሉ፤ ተብሏል።
እስራኤል ባቀደችው መሠረት፣ በጋዛ ላይ የተቀናጀ ወረራ የምትፈጽም ከኾነ፣ ሔዝቦላህ ውጊያውን እንደሚቀላቀል ስጋት በመኖሩ፣ የአሜሪካ ተዋጊ ጄቶች ለመንደርደር ዝግጁ እንደኾኑ ተዘግቧል።
አሜሪካ፣ አልሞ ተኳሽ መሣሪያዎችንና ፀረ ሚሳኤል ተወንጫፊዎችን ለእስራኤል እንደሰጠችና ተጨማሪም እንደምትልክ፣ የመከላከያ ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
መድረክ / ፎረም