የዩናይትድ ስቴትስ እና የሜክስኮ ባለሥልጣናት እየሻቀበ የመጣውን የፍልስተኞች ቁጥር ለመቀነስ ትናንት ረቡዕ ሜክሲኮ ሲቲ ውስጥ ተገናኝተው መክረዋል፡፡
ሁለቱን አገሮች በሚያዋስነው የጋራ ድንበር በኩል በዚህ የታህሳስ ወር ውስጥ በየቀኑ 10ሺ የሚደርሱ ህገወጥ ፍልስተኞች ድንበር አቋርጠው እንደሚገቡ ተነግሯል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ትናንት ከቀትር በኋላ በዚሁ ጉዳይ ላይ ከሜክሲኮ ፕሬዝዳንት አንድሬስ ማኑኤል ሎፔዝ ኦብራዶር ጋር ለሁለት ሰዓታት ያህል ተወያይተዋል፡፡
ከስብሰባው አስቀድሞ የዩናይትድ ስቴትስ ልዑካን በሰጡት መግለጫ፣ ሜክሲኮ ወደ አሜሪካ ደቡብ ምዕራብ ድንበር የሚደርሱትን ስደተኞች ቁጥር ለመገደብ፣ የበለጠ ጥረት ማድረግ እንዳለባት አሳስበዋል።
የሜክስኮ ፕሬዚዳንት ሎፔዝ ኦብራዶር በበኩላቸው፣ ሜክሲኮ ለመርዳት ፍቃደኛ መሆኗን ገልጸው፣ ይሁን እንጂ ግን ከሁለቱ ከፍተኛ የስደተኞች ምንጮች፣ ኩባ እና ቬንዙዌላ ጋር ፣ ዩናይትድ ስቴትስ ያላት ግንኙነት ተሻሽሎ ማየት እንደሚፈልጉ ተናግረዋል፡፡
ለክልሉ ተጨማሪ የልማት እርዳታ እንደሚያስፈልግም ፕሬዚዳንቱ አሳስበዋል፡፡
ኦብራዶር ከስብሰባው በፊት ሲናገሩ "ሁልጊዜ የዚህን ችግር (ፍልሰት) መንስኤዎችን ስለመፍታት እንነጋገራለን፣ ዋናው አስፈላጊው ነገር ግን፣ ድሆቹን ሀገሮች መርዳት ነው" ብለዋል.
አንድ ቀን የፈጀው ወሳኙ ስብሰባ የተካሄደው የፍልስተኞች ቁጥር ከፍተኛው ደረጃ ላይ በደረሰ ጊዜ ነው።
እ.ኤ.አ. በ2023፣ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ፍልሰተኞች፣ ብዙዎቹ ወንጀልን ፣ ድህነትን እና ክልላዊ ግጭቶችን ሸሽተው ከፓናማ እስከ ኮሎምቢያ የተዘረጋውን (ዳሪያን ጋፕ) የተባለውን ጥቅጥቅ ያለ ደን አቋርጠው ወደ መካከለኛው አሜሪካ የገቡ ናቸው፡፡
እኤአ በዚህ መስመር ለመጓዝ የሞከሩት ሰዎች ቁጥር ከቀደመው የ2022 ዓም በእጥፍ የሚበልጥ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ይህ የፍልሰተኞች ቀውስ ለዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን መሰናክል መፍጠሩ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ህግ አውጭዎቹ ሪፐብሊካኑ የምክር ቤት አባላት ለዩክሬን፣ እስራኤል እና ታይዋን የሚሰጡትን ወታደራዊ ድጋፎች በሚያካትተው የስደተኞቹ ህግ ላይ ለውጦችን አድርገዋል፡፡
መድረክ / ፎረም