በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ዩናይትድ ስቴትስ በሱዳን ላይ የጣለችውን ማዕቀቦች ልታላላ ነው


የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽ
የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽ

ዩናይትድ ስቴትስ በሱዳን ላይ ጥላቸው ከቆዩ የገንዘብ ማዕቀቦች አንዳንዶቹን ለማንሳት መወሰኗ ተገለፀ፡፡

ዋይት ሃውስ ይህንን ውሳኔ ዛሬ (ዓርብ) ይፋ ያደርጋል ተብሎ እየተጠበቀ መሆኑን አንድ የአሜሪካ ከፍተኛ ባለሥልጣን ተናግረዋል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ ይህንን ማዕቀቦችን የማቅለል እርምጃ የምትወስደው የሱዳን መንግሥት እያሳየ ነው ለተባሉ ሽብር ፈጠራን በመዋጋት፣ ግጭቶችን በመቀነስ፣ ለደቡብ ሱዳን አማፂያን ከለላና መጠጊያ በመንፈግ፣ ችግር ላይ የወደቁ ሰዎች ሰብዓዊ ድጋፍ እንዲያገኙ በማድረግ በኩል የተሻለ እንቅስቃሴ በማድረግ በሚሰጠው ምላሽ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ በሱዳን ላይ የዛሬ ሃያ ዓመት ማዕቀቦችና የንግድ እገዳ የጣለችው በሰብዓዊ መብቶች አያያዟና ለሽብር ፈጠራ ድጋፍ ትሰጣለች በሚል እንደነበር ይታወሳል፡፡

ዋሺንግተን በወቅቱ የሱዳንን መንግሥት ገንዘብና ሃብቶችም እንዳይንቀሳቀሱ አግዳ ነበር፡፡

ዩናይትድ ስቴትስ የዛሬ አሥር ዓመት በወሰደችው ተጨማሪ እርምጃ መንግሥቱ በዳርፉር ሁከት ውስጥ ተመሣጥሯል በሚል ተጨማሪ ማዕቀቦችን ጥላለች፡፡

ማዕቀቦቹን በሱዳን ላይ እንደ ሀገር፣ እንዲሁም በህዝቡ ላይ አውዳሚ ተፅዕኖ ማሳደራቸውን የገለጡት የሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር አህመድ ቢላል ለቪኦኤ ዘሬ በሰጡት ቃል ዋሺንግተን ማዕቀቦቹን ለማላላት መወሰኗ “አስደሳች ዜና ነው” ብለዋል፡፡

የሕክምና አገልግሎት ለማግኘት ከሀገር መውጣት ባልቻሉ ሰዎችና የቴክኖሎጂ ውጤቶችንም ወደ ሀገር ማስገባት በመቆሙ ማዕቀቦቹ መከራን አስፍነው ቆይተዋል ብለዋል የሱዳኑ የማስታወቂያ ሚኒስትር፡፡

ሚኒስትሩ አክለውም የተለያዩ የቴክኖሎጂ ግብዓቶችን ከአሜሪካ ይገዛ የነበረው የሱዳን አየር መንገድ ከኩባንያዎቹ ጋር መናገድ ባለቻሉ ለመዘጋት መገደዱን አስታውሰው “ማዕቀቦቹ የተነጣጠሩት በመንግሥቱ ወይም በሥርዓቱ ላይ ሳይሆን በሰብዓዊ መብቶች ላይ ነበር” ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የማዕቀቦቹ መነሳት ሱዳንን ከሽብር ፈጠራ ደጋፊ ሀገሮች መዝገብ ውስጥ እንደማያስፍቃት የዩናይትድ ስቴትስ ባለሥልጣናት ጠቁመዋል፡፡

የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር በጦር ወንጀሎችና በጅምላ ፍጅት በዓለምአቀፍ የወንጀል ፍርድ ቤት ይፈለጋሉ፡፡

XS
SM
MD
LG