ዋሽንግተን ዲ.ሲ ላይ ልክ ከሌሊቱ ስድስት ሰዓት ሆኖ አሮጌው 2012 ዓ.ም ለአዲሱ 2013 ዓ.ም ቦታውን ሲለቅቅ በ43ኛው ፕሬዚዳንት ጆርጅ ቡሽ ዘመን ተላልፈው እስከአሁን ሲሠሩ የቆዩት አጠቃላይ የታክስ ወይም የግብር ቅነሣ ድንጋጌዎች ዘመን ያከትማል፡፡
ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የዓመት ገቢያቸው እስከ 250 ሺህ ዶላር በሆነ ቤተሰቦች ላይ የግብር ጣሪያው እንዳይነሣ ከመጀመሪያው የምረጡኝ ዘመቻቸው ጀምሮ ሲጎተጉቱ ቆይተዋል፡፡
ይሁን እንጂ 'በማንም ላይ ታክስ መጨመር የለበትም' በሚሉትና የመንግሥት ወጭዎች በብዙ እንዲቀንሱ የሚፈልጉት ሪፐብሊካን እንደራሴዎች ከፕሬዚዳንቱና ከዴሞክራት የሕግ መምሪያና የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቶች አቻዎቻቸው ሃሣብ ጋር ሣይስማሙ በመቆየታቸው እስከአሁኑ የሰዓት ገደብ ድረስ መግባባት ሣይደረስ ቆይቷል፡፡
ከገና ማግሥት እረፍታቸውን አቋርጠው ወደ ሥራቸው የተመለሱት ፕሬዚዳንቱና እንደራሴዎቹ ዛሬም ሙሉ ቀን ሲሟገቱ ቢውሉም የሕግ ረቂቅ እንዲያቀርብ ሲጠበቅበት የዋለው የሕግ መወሰኛ የመጨረሻ ስምምነት ላይ ሳይደርስና ድምፅም ሳይሰጥ በማምሸቱ የተወካዮች ምክር ቤቱ አባላት በዛሬ የሴኔቱ ሰነድ ላይ ድምፅ ለመስጠት ነገ በአዲሱ ዓመት ከቀኑ ስምንት ሰዓት ላይ ድምፅ ለመስጠት ተመልሰው ለመገናኘት ተነጋግረው ተለያይተዋል፡፡
ይህ ሁኔታ በመሠረተ-ሃሣብ ደረጃ ዩናይትድ ስቴትስ የጊዜ ገደቧን አለመጠበቋን እና ሲሠጋበት የቆየውን የበጀት አፋፍ ማለፏን ያሣያል እያሉ ተንታኞች እና መገናኛ ብዙኃን እየተናገሩ ነው፡፡
ይሁን እንጂ ቀደም ሲል “ሁሉም የፈለገውን ሁሉ አያገኝም” ያሉት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ አቋማቸውን አለሣልሰው አስቀምጠውት የነበረውን የገቢ ጣሪያ ለቤተሰብ ወደ 450 ሺህ ዶላር የግል ገቢ ከሆነ ደግሞ ወደ 400 ሺህ ዶላር ከፍ እንዲል መስማማታቸውን አሣውቀዋል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ የፕሬዚዳንቱ አቋም ጣሪያው ከ250 ሺህ ዶላር ከፍ ማለቱን የማይፈልጉ ብዙ የዴሞክራቲክ ፓርቲውን ሰዎቻቸውን ቅር እንዳሰኘ ይሰማል፡፡
ዘግይቶ ከዋይት ሃውስና ከኮንግረሱ እየወጡ ያሉ ዘገባዎች እንደሚጠቁሙት የሕግ መወሰኛው የሁለቱም ወገን መማክርት ለነገው የተወካዮች ምክር ቤቱ ስብሰባ የሚያቀርቡት አግባቢ ሃሣብ ላይ መድረሣቸው ተሰምቷል፡፡
በዚህ የስምምነት ሃሣብ መሠረት አሜሪካ ከበጀት አፋፏ ከወደቀች ከአዲስ ዓመት ማግስት፣ ማለትም ከረቡዕ ታኅሣስ 24 ጀምሮ ተግባራዊ የሚሆነውን የመንግሥቱን አጠቃላይ ወጭ ቅነሣ ለሁለት ወራት ለማዘግየት የሚያስችል ስምምነት እንደሚገኝበት ታውቋል፡፡
ገና በይፋ ባልተገለፀ ስምምነት በዴሞክራቱና በሪፐብሊካኑ ሴናተሮች መካከል የተደረሰና ዴሞክራቶቹ መሪዎች የተወካዮች ምክር ቤቱ የአናሣ መሪ ናንሲ ፔሎሲ፣ የሴኔቱ አብዝኀ መሪ ሃሪ ሪድ እና ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ የፈረሙበት፣ እንዲሁም የሴኔቱ አናሣ አባላት መሪ ሚች ማክኮኔል እንደተስማሙበት የተነገረው ሠነድ በነገው የተወካዮች ምክር ቤቱ የከሰዓት በኋላ ስብሰባ ካልፀደቀ ከታኅሣስ 23 ጀምሮ በሁሉም የአሜሪካ ግብር ከፋዮች ላይ እስከአሁን እየሠራ ያለው የታክስ ታሪፍ ከ35 ከመቶ ወደ 39.5 ከመቶ ያሻቅባል፡፡
ይህም በዓመት ሃምሣ ሺህ ዶላር ገቢ ባላቸው ቤተሰቦች ላይ ግብሩ በ2000 ዶላር፣ እስከ 75 ሺህ ዶላር በሚያገኙ ላይ 3 ሺህ 500፣ እንዲሁም ሁለት መቶ ሃምሣ ሺህ ዶላር በሚያገኙ ላይ ደግሞ የስምንት ሺህ ዶላር የታክስ ጭማሪ ይከተላል፡፡
ወገኖቹ ስምምነት ላይ እንደሚደርሱ ተስፋ እንዳላቸው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሰኞ ከቀትር በኋላ ሰጥተውት በነበረ ጋዜጣዊ መግለጫ መናገራቸው ይታወሣል፡፡
አሁን ባለው ሁኔታ እንኳ ብዙዎች ቀነ ገደቡ ወይም ሰዓቱ “በመሠረቱ አልፏል” ብለው እየተጨነቁ ያሉ ብዙ ቢሆኑም ሁኔታዎችን ለማስተካከል “አሁንም ገና ጨርሶ አልመሸም” የሚሉትና የፕሬዚዳንቱ ተስፋ ሣይሰምር ቀርቶ ነገ የተወካዮች ምክር ቤቱ “የረፈደ ሰዓት መድኅን” የሚሆን ውሣኔ ካላሣለፈ ሁኔታው የገዥዎችን የማውጣት አቅምና ፍላጎት ይቀንሣል፤ የመንግሥቱ ወጭ ወዲያው በከፍተኛ መጠን ይቀንስና መንግሥቱ እጅግ በርካታ መርኃግብሮቹን ለመዝጋት፤ ሠራተኞቹን ከሥራ ያለክፍያ ለማስቀረት አለበለዚያም ለማስወጣት ይገደዳል፤ እስከ አሁን ሲከፍል የነበረውን የሥራ አጥነት ክፍያ ያቆማል፣ በዚህም አሁን በድጋፍ ላይ ያሉ ሁለት ሚሊየን ሰዎች ክፍያቸው ከዚህ ወር ጀምሮ ይሠረዛል፡፡ ሁኔታው የዓለም ገበያዎችን ያዳክምና የዩናይትድ ስቴትስ ምጣኔ ኃብት ቀደም ሲል ከነበረበት ወደባሰ ቀውስና አዘቅት ይገባል፤ ተያይዞም የዓለም ምጣኔ ኃብት ለከፋና ለአስጊ ጉዳት ይዳረጋል - የሁሉም ፖለቲከኞችና የአብዛኛው የምጣኔ ኃብት ጠቢባን አጠቃላይ ሥጋት ነው፡፡
አፋፍ ላይ ካሉ ሌሎች የበጀት ጉዳዮች መካከል ባለፈው ዓመት እንዲሁ በፖለቲካው ሰዎች ያልተቋረጡ ንትርኮች ምክንያት ቀነ ገደቡ በመድረሱ ምክንያት የዩናይትድ ስቴትስን የተበዳሪነት መልካም ዝና በአነስተኛ ነጥብም ቢሆን እንዲቀንስ ያደረገውን ዓይነት የብድር ጣሪያዋን ከፍ የማድረግ ድርድር ይገኝበታል፡፡ መጭው የብድር ጣሪያ ከፍ እንዲደረግ የሚጠበቅበት ጊዜ የቀሩት ሁለት ወራት ብቻ ናቸው፡፡
//ይቀጥላል ….//