በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዘዳንት Barack Obama የአሜሪካን በሊቢያ ወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ተከላክለዋል።


ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ በንግግራቸው፥ በሊቢያ ላይ ለምን ከዚህ ውሳኔ እንደደረሱ፥ እስካሁን ስለተገኙ ስኬቶችና ለአሜሪካ ወታደራዊ ኃይል ይሰጣል ስላሉት ጥቅምና ዩናይትድ ስቴትስ በስፋት ስለምትጫወተው መሪ ሚና አብራርተዋል።

ዩናይትድ ስቴትስና ሸሪኰቿ በሊቢያ ጣልቃ የገቡት አሉ ፕሬዘዳንት ኦባማ፥ ጣልቃ የገቡት የሞዓማር ጋዳፊ ኃይሎችን «አረመኔአዊ ጭቆናና» በሲቪሎች ላይ እያደረሱ የነበረውን ፍጅት ለማስቆም እንዲሁም አገሪቱ ላይ ያንዣብብ የነበረውን ሰብዓዊ ቀውስ ለመከላከል ነው ብለዋል።

ሚስተር ኦባማ ንግግራቸውን በመቀጠል፥ ዩናይትድ ስቴትስ በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ከዓለምአቀፍ አጋሮች ጋር በመሆን ስፋት ያለው ጥምረት ለማቋቋም፥ የሊቢያ ሲቪሎችን ደህንነት መጠበቅ የሚያስችል የዓለሙን ድርጅት ሥልጣን ለማግኘትና ከበረራ የተከለከለ ቀጣና ለመመሥረት ችላለች ብለዋል።

ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ በትላንቱ ንግግራቸው ታዲያ ምንም እንኳ ሊቢያና ዓለማችን ያለ ሞዓማር ጋዳፊ የተሻሉ መሆናቸው ባያጠያይቅም በወታደራዊ ኃይል የመንግሥት ለውጥ ለማምጣት እንደማይፈልጉ ግን አስረድተዋል።

« ጋዳፊን በኃይል ለመጣል ብንሞክር ኖሮ፥ ህብረታችን ይሰነጣጠቅ ነበር። የዩናይትድ ስቴትስ እግረኛ ወታደሮችን መመደብ ደግሞ በሠራዊታችን ደህንነት ላይ ከፍተኛ አደጋን መጋበዝ ይሆናል። ወጪውም እንደዚያው የበዛና የቀጣይ ጊዜ ኃላፊነታችንም ከባድ ይሆን ነበር »

ዩናይትድ ስቴትስ አሉ ፕሬዘዳንት ኦባማ በዚያ የከፋ ገዳና አልፋለች። በኢራቅ በሺዎች የሚቆጠር ያሜሪካና ኢራቃውያን ዜጐች ሕይወት ጠፍቷል። በገንዘብም አንድ ትሪሊዮን ዶላር ተከፍሏል። እናም ይህን ጐዳና በሊቢያም ደግመን አንጓዝም።

ፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ ቀደም ሲል ከፈረንሳዩ አቻቸው ኒኰላስ ሳርኰዚ፥ ከጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ መርክል እና ከብሪታንያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካምረን ጋር መነጋገራቸውን የዋይት ሐውስ ቤተ መንግሥት አስታውቋል።

መሪዎቹ ሚስተር ጋዳፊ ሥልጣን መልቀቅ እንዳለባቸውና የሊቢያ ሕዝብ መፃዒ የፖለቲካ ዕድሉን እራሡ ሊወስን እንደሚገባ መስማማታቸውን ያወጡት መግለጫ ያስረዳል።

ተመሳሳይ ርእስ

XS
SM
MD
LG