በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩዎች ፊት ለፊት ተገናኙ፤ ክርክሩ የሞቀ ነበር


የሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጩ የቀድሞ የማሳቹሴትስ ገዥ ሚት ራምኒ እና የዴሞክራቲክ ፓርቲው ዕጩ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ
የሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጩ የቀድሞ የማሳቹሴትስ ገዥ ሚት ራምኒ እና የዴሞክራቲክ ፓርቲው ዕጩ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ

የፊታችን ጥቅምት 27/2005 ዓ.ም ለሚካሄደው ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ የሚፎካከሩት የዴሞክራቲክ ፓርቲው ዕጩ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እና የሪፐብሊካን ፓርቲው ዕጩ የቀድሞ የማሳቹሴትስ ገዥ ሚት ራምኒ የመጀመሪያውን የፊት ለፊት ክርክር አካሄዱ፡፡



please wait

No media source currently available

0:00 0:07:47 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ

please wait

No media source currently available

0:00 1:32:40 0:00
ቀጥተኛ መገናኛ



በምዕራባዊቱ የዩናይትድ ስቴትስ ግዛት ዴንቨር ዋና ከተማ ኮሎራዶ በሚገኘው የዴንቨር ዩኒቨርሲቲ ውስጥ የተካሄደውን የረቡዕ መስከረም 23 ምሽት ክርክር የከፈቱት ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ሲሆኑ እርሣቸው ወደ ፕሬዚዳንትነቱ በመጡበት ጊዜ ውድቀት ውስጥ የነበረውና እየታገለ ያለው የሃገራቸው ምጣኔ ሃብት ወደ ነበረበት ጥንካሬው ለመመለስ እየታገለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡


ይሁን እንጂ እጅግ በጣም ብዙ ሥራ ወደፊት እንደሚጠበቅ አመልክተው በትምህርትና በሥልጠናዎች ላይ መዋዕለ ነዋይ ማፍሰስ እና የታክስ ቅነሣ ማድረግ ለሃገራቸው የተሻለው አማራጭ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ገልፀዋል፡፡



ተቀናቃኛቸው ሚት ራምኒ ደግሞ ሃገራቸው ከቀደመው የተለየ መንገድ መከተል እንዳለባት አሳስበው ከሚስተር ኦባማ የተሻለ ነው የሚሉት የእርሣቸው ዕቅድ የኢነርጂ ልማትን በከፍተኛ ሁኔታ ማሣደግ፣ የበለጠ የዓለምአቀፍ ንግድ መስኮችን መክፈት፣ የበለጡ የሥራ ሥልጠናዎችን ማስፋፋት፣ የበጀት ጉደለቱን መቀነስ እና የአነስተኛ ቢዝነሶችን መስፋፋት መደገፍን እንደሚያቅፍ አመልከተዋል፡፡

ፕሬዚዳንት ኦባማ ለግዙፎቹ ኩባያዎችም የታክስ ቅነሣ እንደሚያደርጉ ገልፀው የሥራ ዕድሎችን ወደ ውጭ ሊያስኮበልሉ የሚችሉ ክፍተቶችን ሁሉ እንደሚዘጉ ተናግረዋል፡፡ የወደፊቱ የኢነርጂ ማስፋፊያ ዕቅድም የነፋስ፣ የፀሐይ ኃይልና ባዮፍዩልስን ማካተት እንደሚኖርበት ገልፀዋል፡፡

እነዚህን የመሠረተ ልማት ዕቅዶች ወደ ተግባር ለመመንዘር ግን መካከለኛ ገቢ ባለው አሜሪካዊ ላይ ተጨማሪ ጫና መጣል እንደማይኖርበትም ኦባማ አሳስበዋል፡፡

ሚት ራምኒ ደግሞ ይህ መካከለኛ ገቢ ያለው አሜሪካዊ በታክሶች ቁልል ሥር “ተቀብሯል”፣ “ተጨፍልቋል” ብለዋል፡፡ በመሆኑም የታክስ መጠኑ ለግለሰቦችም ለኩባንያዎችም ሊቀልላቸው እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

የመንግሥት ቀዳሚ ሚና የሕዝቡን ደህንነት ማስጠበቅ መሆኑን ፕሬዚዳንት ኦባማ ጠቁመው ሕዝቡ የስኬት ሕይወት መምራት እንዲችልም አመቺ ሁኔታዎችን ማዘጋጀት እንደሚኖርበት ገልፀዋል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ባለፈው ጊዜ እንደ ሐዲዶችን መዘርጋት፣ የትምህርትና የምርምር ተቋማትን መገንባትና ማስፋፋትን በመሳሰሉ መስኮች እገዛ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

ሚስተር ራምኒ ደግሞ የመንግሥት ሚና ሕገመንግሥቱንና የነፃነት አዋጁን መርሆዎች ማስከበር እና መንከባከብ መሆናቸውን ገልፀው ይህም ሊጨበጥ የሚችለው ወታደራዊ ጥንካሬን በማረጋገጥ፣ ለእምነት መቻቻል ቁርጠኝነትን በማሣየት፣ ለአዛውንትና የአካል ጉዳት ላለባቸው እንክብካቤን በማድረግ፣ ግለሰቦች ሕልሞቻቸውን እውን እንዲያደርጉ ነፃነቶቻቸውን በማስጠበቅ መሆኑን አስረድረተዋል፡፡

ፕሬዚዳንቱ በመዝጊያ ንግግራቸው መጭዎቹን ዓመታት እስከአሁን በነበሩት የአራት ዓመታት የዋይት ሃውስ የጥንካሬያቸው ውጤት ላይ ማቆም እንደሚፈልጉ ገልፀው በሁለተኛው የሥልጣን ዘመናቸውም እንደመጀመሪያው ሁሉ በርትተው እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡

ሚስተር ራምኒ ደግሞ በመዝጊያ ንግግራቸው ያለፉትን ዓይነት አራት ተጨማሪ ዓመታት ማለት ለባለ መካከለኛው ገቢ አሜሪካዊ ተጨማሪ ከባድ ዘመናት ማለት ናቸው ብለዋል፡፡ እርሣቸው ቢመረጡ 12 ሚሊየን ተጨማሪ የሥራ ዕድሎችን እንደሚከፍቱ፣ የፕሬዚዳንቱ መለያ የሆነውን የጤና ጥበቃ ማሻሻያ ሕግ እንደሚሠርዙና በሌላ እንደሚተኩ ቃል ገብተው የወታደራዊ ወጭ ቅነሣ እንደማያደርጉ ግን አስረድተዋል፡፡

ሁለቱ ዕጩዎች የፊታችን ጥቅምት 6 ደግሞ በስብሰባ አዳራሽ ውስጥ ከሕዝብ ጋር ተገናኝተው በሚካሄድ የክርክር ዓይነት እንደገና የሚጋጠሙ ሲሆን በዚያ ወቅት ከታዳሚውም ለሚቀርቡላቸው ጥያቄዎች መልስ ይሰጣሉ፡፡

ከዛሬ በኋላ የጥቅምት ስድስቱን ጨምሮ ሁለት በፕሬዚዳንታዊ ዕጩዎቹና አንድ በምክትል ፕሬዚዳንት ዕጩዎቹ መካከል የሚካሄዱ ክርክሮች እንደሚኖሩ በዕቅድ ተይዟል፡፡




ተጨማሪና ዝርዝር ዘገባዎች በቅርቡ ይወጣሉ፡፡
XS
SM
MD
LG