በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለአሜሪካ ዜግነት የሚሰጠው ፈተና ሊቀየር ነው


የአሜሪካ ዜጋ የመሆን ሥነ ስርዓት እያካሄዱ
የአሜሪካ ዜጋ የመሆን ሥነ ስርዓት እያካሄዱ

የአሜሪካ ዜግነትን ለማግኘት የሚሰጠው ፈተና በአዲስ መልክ ሊዘጋጅ መሆኑ ታውቋል። አንዳንድ ውጭ ሀገር ዜጎች እና የስደተኞች መብት አቀንቃኞች ግን፣ አዲሱ ለውጥ ዝቅተኛ የቋንቋ ችሎታ ያላቸውን ሰዎች ሊጎዳ ይችላል የሚል ስጋት አላቸው። ፈተናው የአሜሪካ ዜጋ ለመሆን መከናወን ካለባቸው ተግባራት አንዱ ነው።

የቀድሞው ፕሬዝደንት ዶናልድ ትረምፕ፤ ከሶስት ዓመታት በፊት፣ ፈተናው ረጅም እና ለማለፍ አዳጋች እንዲሆን ካስደረጉት በኋላ፣ በርካቶች የዜግነት ጥያቄያቸው ተስተጓጉሏል። ለጥቀው የመጡት ጆ ባይደን ግን ሥልጣኑን በያዙ በወራት ውስጥ ዜግነትን ለማግኘት በሚደረግ ሂደት ውስጥ ያሉ እንቅፋቶች እንዲነሱ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል። በዚህም መሠረት የዜግነት ፈተናው ወደቀድሞው ተመልሶ ነበር።

ባለፈው ህዳር ግን፣ ለ15 ዓመት የዘለቀው ፈተና ሊከለስ እንደሚገባው ባለሥልጣናት አስታውቀዋል። አዲሱ ፈተና በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት መጨረሻ እንደሚጀምር ይጠበቃል።

በአዲሱ ፈተና፣ ለቋንቋ ችሎታ ትኩረት ይሰጣል ተብሏል። ፈታኙ የአሜሪካን የዘወትር ክንውኖችን ወይም ሁኔታዎችን ለተፈታኞች በፎቶ ያቀርባል፣ ተፈታኞች ያዩትን በእንግሊዝኛ እንዲገልጹ ይጠየቃሉ። ፈታኙም የአመልካቹን የቋንቋ ችሎታ ይገመግማል።

ባለፈው ግንቦት ዜግነት ያገኘችውና፣ ከ10 ዓመት በፊት ከኢትዮጵያ የመጣችው የ32 ዓመቷ ሄቨን ምህረታ “ፎቶን ተመልክቼ ምንነቱን በእንግሊዝኛ መግለጽ ሊከብደኝ ይችል ነበር” ብላለች።

ከተለመደው ጥያቄ ውጪ የቋንቋ ችሎታም መካተቱ እንደሷ ላሉ ስደተኞች ፈተናውን እንደሚያከብደው ሄቨን ጨምራ መግለጿን የአሶስዬትድ ፕረስ ሪፖርት አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG